ከሐምሌ 26 – ነሐሴ 2 2006 ዓ.ም
ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ዮሐ. 3፡1-15፣ ማቴ. 13፡33፣ 2ኛ ቆሮ. 5፡17፣ ዮሐ. 15፡4-10 ማቴ. 6፡9-13፣ ሉቃ. 9፡23, 24ን ያንብቡ፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ፡- “ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡ (ዮሐ. 3፡3)
ኒ ቆዲሞስ ወደ ክርስቶስ የተሳበ ቢሆንም በግልጽ ወደ እርሱ ለመሄድ ግን አልደፈረም፡፡ ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር መሆኑን እውቅና በመስጠት ሰላምታ ሰጠው፡፡ ጌታም ከዚህ መልካም ሰላምታ በስተጀርባ እውነት ፈላጊ መኖሩን ተረድቶ፣ ጊዜ ሳያባክን ኒቆዲሞስ የቃል እውቀት ሳይሆን መንፈሳዊ ለውጥ፣ ያም አዲስ ህይወት እንደሚያስፈልገው ነገረው፡፡
ሐሳቡም ለኒቆዲሞስ ለማስተዋል አስቸጋሪ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአብርሃም ዘር በመሆኑ በእግዚአብሔር መንግሥት ሥፍራ እንደሚኖረው እርግጠኛ ነበር፡፡ በተጨማሪም እንደ ጠንቃቃ ፈሪሳዊነቱ በእግዚአብሔር ተቀባይነት ማግኘት አለበት አይደል? ታዲያ ይህን የመሰለ ፍጹም ለውጥ ለምን አስፈለገው?
ኢሱስም መንፈሳዊ ለውጥ ከሰው አቅም በላይ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ የሚተገብረው ነገር መሆኑን በትዕግሥት አስረዳው፡፡ ምንም እንኳን እንዴት እንደሚከሰት የማናየውና የማናስተውለው ቢሆንም ውጤቱን ግን ማየት እንችላለን፡፡ ይህንንም መመለስ በክርስቶስ አዲስ ህይወት ብለን እንጠራዋለን፡፡
እግዚአብሔር እንዴት እንደጠራንና እንደለወጠን ሁልጊዜ የምናስታውስ ቢሆንም የእኛ የየዕለት ግድድሮሻችን የሚሆነው በእርሱ ሥር ሰደን እንድንጸናና ራሱን ወደ መምሰል እንዲለውጠን ይሆናል፡፡
የዚህን ሳምንት ትምህርት ለ ነሐሴ 3 ሰንበት አጥንተው ይዘጋጁ፡፡
እሁድ ሐምሌ 27 2006 ዓ.ም
እንደገና መወለድ
አንድ ቀናኢ ክርስቲያን አንዲትን ፖለቲከኛ “እንደገና ተወልደሻልን?” በማለት ጥያቄ አቀረበላት፡፡ እርሷም (ፖለቲከኛዋም) ጥያቄው የግሏ እንደሆነ የወሰነችው በመሆኑ በቁጣ “የመጀመሪያው በቂ ነው አመሰግናለሁ፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡
በቂ ሊሆን ይችል ይሆናል፣ የወደቀውን የእኛን ፍጥረት በሚመለከት ግን፣ የመጀመሪያ መወለዳችን ቢያንስ ለዘላለም ህይወት አያበቃንም፡፡ ለዚህ ሲባል “ዳግም መወለድ” ይኖርብናል፡፡ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር ያደረገውን ንግግር በዮሐ. 3፡1-5 ያንብቡ፡፡ ዳግም መወለድን ክርስቶስ ያብራራው እንዴት ነበር፡፡
ኒቆዲሞስ የእሥራኤል መምህር እንደመሆኑ የአዲስ ልብን አስፈላጊነትና አዲሱን ልብ በውስጣችን ለመፍጠር እግዚአብሔር ያለውን ፈቃደኝነት የሚናገሩ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማወቁ አያጠራጥርም (መዝ. 51፡1ዐ፣ ህዝ. 36፡26)፡፡ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስረዳው ይህንን እውነትና እንዴት ሊሆን እንደሚችል ነበር፡፡
ዮሐንስ እንደዘገበው ንግግሩ የሚያበቃው በየሱስ ቃላት ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም ምላሽ አልሠጠም፡፡ ምናልባትም ወደ ቤቱ የተመለሰው ጥልቅ በሆነ ቁዘማ ተውጦ ሊሆን ይችላል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጡ በዝግታ ሠርቶ፣ ከሦስት ዓመት በኋላ ሳይወድ በግድ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆነ፡፡
ዳግም የመወለዱ አስፈላጊነት ያለ ጥርጥር የሚያሳየን ነገር ከመንፈሳዊ አንፃር የመጀመሪያ መወለድ በቂ አለመሆኑን ነው፡፡ አዲስ መወለድ እጥፍ ነው፤ ያም ከውኃና ከመንፈስ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ባስተማረው መሠረት፣ ለኒቆዲሞስ ከውሃ መወለድ መጠመቅ መሆኑን በቀላሉ ያስተውለዋል፡፡ ሌላኛው እርሱ እንዲያውቀው የተፈለገው ከመንፈስ መወለድ ማለት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የልብ መለወጥ መሆኑን ነው፡፡
በአካል መወለድና በመንፈስ መወለድ ተመሳሳይነቶች አሏቸው፡፡ ሁሉ የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የትኛውንም ውልደት በራሳችን አንፈጽመውም፤ ለእኛ የተሠራልን ነው፡፡ ነገር ግን በመካከላቸው በጣም አስፈላጊ የሆነ ልዩነትም አለ፤ በአካል ለመወለዳችን ምንም ዓይነት ምርጫ ማድረግ አንችልም፤ በመንፈስ ለመወለድ ግን መምረጥ እንችላለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው አዲስ መንፈሳዊ ማንነትን እንዲፈጥርላቸው በነፃነት ለመንፈስ ቅዱስ ራሳቸውን የሚሠጡ ብቻ አዲስ መወለድ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ሊለውጠን የሚጓጓ ቢሆንም ነፃነታችንን የሚያከብር በመሆኑ በግድ አይለውጠንም፡፡
እግዚአብሔር እንዴት እንደለወጥዎ ያስቡ፡፡ ብዙ ታሪካዊ ሂደትን ያለፈ፣ ረዥምና ለማስተዋል አስቸጋሪ በሆነ መንገድ እንኳ ቢሆን ችግር የለውም አዲሱን መወለድ እንዴት አዩት?
________________________________________________________________
________________________________________________________________
ሰኞ ሐምሌ 28, 2ዐዐ6 ዓ.ም
አዲስ ህይወት በክርስቶስ
እንደገና መወለድ የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ብቻ ነው፡፡ እየሱስ ክርስቶስ የግሪኩን ቃል (pneuma) “መንፈስ እና “ነፋስ” በሚለው ትርጓሜ የመለወጥ ሂደት ምሳሌ አድርጐ ተጠቅሟል፡፡ (ዮሐ. 3፡8)፡፡ ነፋስ ማናችንም ሳናስጀምረው፣ የሚሄድበትን አቅጣጫ ሳንመራው ወይም ሳናስቆመው ይነፍሳል፡፡ የእርሱም ታላቅ ኃይል ከሰብዓዊ ቁጥጥር በላይ ነው፡፡ ለእርሱም ልንሰጠው የምንችለው ምላሽ ቢኖር መከላከል ወይም ያለውን ጉልበት ለጥቅማችን እንዲሆን አድርገን መጠቀም ነው፡፡
ልክ እንደዚሁ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ በመሆን ወደ ክርስቶስ እንዲሳብ የማድረግ ሥራን ይሠራል፡፡ ማንም በእርሱ የማዳንና የመለወጥ ታላቅ ሥራ ላይ ኃይል የለውም ልንቃወመው ወይም በእርሱ ልንፀና እንችላለን፡፡ ለሚለውጠን ለእርሱ ተጽዕኖ ራሳችንን ከሠጠነው መንፈስ ቅዱስ አዲስ ህይወት በእኛ ይፈጥራል፡፡
የአዲስ ህይወት ልምምድ ያለን መሆኑን የምናውቅበት መንገድ አለን? አዎ፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ሳይታይ ቢሆንም የእርሱ ተግባራት ውጤቶች የሚታዩ ናቸው፡፡ በዙሪያችን የሚገኙ ክርስቶስ አዲስ ልብ እንደፈጠረ ያውቃሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ
እርሱ በውስጣችን የሚያደርገው ለውጥ ውጤቶች የሚሆኑ ውጫዊ መገለጫዎችን ያፈራል (ይፈጥራል)፡፡ ክርስቶስ እንዳለው (ማቴ. 7፡2ዐ) “በፍሬያቸው ታውቁዋቸዋላችሁ፡፡”
በክርስቶስ የሆነ አዲስ ህይወት ሁለመናንን የሚያጠቃልል ጥቂት ውጫዊ የሆነ ለውጥ አይደለም፡፡ የነበረው አሮጌ ህይወት ማሻሻያ ወይም ለውጥ ሳይሆን ነገር ግን ፍጹም ለውጥ ነው፡፡
የሚከተሉት ጥቅሶች አዲሱ ውልደት በህይወታችን ስለሚያከናውነው ተግባር ምን ይነግሩናል? ቆሮ. 3፡5-7፣ ገላ. 6፡15፡፡
________________________________________________________________
________________________________________________________________
ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በውስጣችን አዲስ አስተሳሰብ፣ ስሜትና አዲስ እይታን ይተክላል፡፡ እርሱ ህሊናችንን ይቀሰቅሰዋል፣ አእምሮአችንን ይለውጣል ያልተቀደሱ ፍላጐቶቻችንን ሁሉ እንዲለሰልሱ በማድረግ በጣፋጭ ሰማያዊ ሰላም
ይሞላናል፡፡ ለውጥ በአንዴ የማይመጣ ነገር ቢሆንም በጊዜ ሂደት በክርስቶስ አዲስ ፍጥረታት እንሆናለን፡፡ ልንለወጥ ይገባል፤ ምክንያቱም መሠረታዊው (የመጀመሪያው) ትውልዳችን ከእግዚአብሔር ጋር የሚስማማ ስላልሆነ ይህ ሊሆን ግድ ነው፡፡
ያለፉትን ሃያ አራት ሰዓታት ህይወትዎን ያስለስሉ፡፡ እርስዎን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች በእርስዎ ቃላት፣ ባህርይ እና ድርጊት ክርስቶስን ምን ያህል ሊያዩ ቻሉ? ለእነዚያ አሁንም ለውጥ ለሚያስፈልግዎ ባህሪያት ይፀልዩ፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 29 2ዐዐ6 ዓ.ም
በክርስቶስ መጽናት
ሁሌ የሚለመልም መንፈሳዊ ህይወት ሊኖረን የሚችለው ሳናቋርጥ በክርስቶስ ላይ በመደገፍ ብቻ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊፈጸምልን እንደሚችል ለማሳየት ክርስቶስ የወይኑን ምሳሌ ተጠቅሟል፡፡ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” (ዮሐ. 15፡5) በብሉይ ኪዳን ዘመን እሥራኤላውያን እግዚአብሔር የተከለው ወይን ማሳያ ነበሩ ኢሳ. 5፡1-7፣ መዝ. 80፡8,9፣ ኤር. 2፡21,?)፣ ነገር ግን ክርስቶስ ራሱን እንደ “እውነተኛ የወይን ግንድ” መስሏል (ዮሐ. 15፡1) እናም ደቀመዛሙርቱን ልክ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ እንደተጠበቀ ሁሉ እነርሱም ከእርሱ ጋር አንድ እንዲሆኑ ያደፋፍራቸዋል፡፡
እነዚህ ጥቅሶች ሳያቋርጡ በክርስቶስ ስለ መጽናት (ስለ መጣበቅ) ምን ይነግሩናል? (ዮሐ. 15፡4-10)፡፡
________________________________________________________________
________________________________________________________________
በቅርቡ ከግንዱ የተቆረጠ ቅርንጫፍ ለጊዜው ህይወት ያለው ቢመስልም በእርግጥ ከህይወት ምንጭ በመቆረጡ ይሞታል፡፡ ይደርቃል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እኛ በህይወት ልንኖር የምንችለው ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ ውጤታማ ለመሆን ይህ ህብረት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የጧት የፀሎት ጊዜ አስፈላጊ ነው፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን አንድነት ቀኑን ሁሉ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በክርስቶስ መጽናት ማለት እርሱን ሳያቋርጡ መፈለግ የእርሱን ምሪት መጠየቅ የእርሱን ፈቃድ ለመታዘዝ እንዲያስችለን መጸለይ እና የእርሱ ፍቅር እንዲሞላን መለመን ማለት ነው፡፡
አታላይ ከሆኑ ወጥመዶች አንዱ ከእግዚአብሔር የተለየን ክርስቲያናዊ ህይወት ለመኖር መሞከር ነው፡፡ “ያለ እኔ አንዳች ልታደርጉ አትችሉም” (ዮሐ. 15፡5)፡፡ ያለ እርሱ አንዳች ፈተና ልንቋቋም አንችልም አንዳችም ኃጢአት አናሸንፍም ወይም እርሱን የሚመስል ባህሪይ ልንለማመድ አንችልም፡፡ አዲሱ መንፈሳዊ ህይወት ሊያድግ የሚችለው ባልተቋረጠ ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን ህብረት ብቻ ነው፡፡
ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል እንበለጽጋለን፡፡ እናድጋለን፡፡ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል “እኔ ለእናንተ የምናገራቸው ቃላት መንፈስና ህይወት ናቸው (ዮሐ. 6፡63)፡፡ እነዚህ ቃላት በልባችንና በአእምሮአችን ሲከማቹ እኛን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ህብረት እንድንቆይ በማድረግ ፀሎታችንን የተነቃቃ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ “በዚህ ዓለም ሀሳብ” ለመታለል ቀላል ቢሆንም (ማር. 4፡19)፣ በክርስቶስ ፀንተን ለመቆየት በትኩረት ጥረት ልናደርግ ይገባናል፡፡
ቀጣይነት ባለው መልኩ በክርስቶስ ፀንተው እንዳይቆሙ የሚያደርግዎት ምን ይሆን? እነርሱን ለማስወገድ ወይም ለማሸነፍ ምን እርምጃዎችን ይወስዳሉ?
ረቡዕ ሐምሌ 3ዐ, 2006 ዓ.ም
ፀሎት
በመንፈስ ለማደግና በክርስቶስ ለመጽናት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተጨማሪ ፀሎት አስፈላጊ ነው፡፡ ክርስቶስ ራሱ እንኳ ከአባቱ ጋር ለመተባበር ፀሎት አስፈልጐት ነበር፡፡ የፀሎትን ህይወት ለእኛ ምሳሌ ትቶልናል፡፡ ፀሎት የእርሱን በጣም ወሳኝ የሆኑ የሕይወት ምዕራፋት መለያ ነበር፡፡ በጥምቀቱ ጊዜ ፀልዮአል፡፡ከመንጋቱ በፊት ብቻውን ወይም ከፀሐይ ግባት በኋላ በተራሮች ላይ ፀልዮአል፡፡ አልአዛርን ከሞት ለማንሳት ፀልዮአል፡፡ መስቀል እንኳን እንዳይፀልይ ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡
“አባት የሚያስፈልገንን ሳንጠይቀው ቀድሞ የሚያውቀው” ከሆነ (ማቴ. 6፡8) የሚያስፈልገንን በፀሎት መጠየቁ ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም በፀሎት በኩል (አማካይነት) ራሳችንን ባዶ ማድረግና በእርሱ ላይ በፍጹም መደገፍን እንማራለን፡፡
የክርስቶስ ተስፋ እንዲህ ይላል፡፡ “ጠይቁ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል (ማቴ. 7፡7)፡፡መጨረሻ በሌላቸው ከንቱ ቃላት የእርሱን ልብ ለማግኘት ባያስፈልገንም (ማቴ. 6፡5-9) ምንም ቢሆን ሳንሰለች መፀለይና ተስፋዎቹን የሙጥኝ ማለት ይገባናል (ዮሐ. 15፡7፡16፡24)
ጌታችን ያስተማረን ፀሎት የተለያዩ ክፍሎች በእርሱ እንድናድግ የሚረዱን እንዴት ነው? ማቴ. 6፡9-13ን ተመልከቱ፡፡
እየሱስ በሰማይ አማላጃችን ነው፡፡ ስለዚህ ፀሎታችንን በእርሱ በኩል ወደ አባቱ እንድናደርስ አስተምሮናል፡፡ “በእውነት እላችኋለሁ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አባቴ ያደርግላችኋል፡፡ (ዮሐ. 16፡23)፡፡ ይህ አስደናቂ የሆነው ተስፋ ተፈጻሚ እንዲሆን
የሚያስፈልጉን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ነግሮናል፡፡ እግዚአብሔር ሊመልስልን እንደሚችል ማመን ይገባናል (ማቴ. 21፡22)፡፡ ባልንጀራችንን ይቅር የሚል ዝንባሌ (ባህርይ ያስፈልገናል (ማር. 11፡25)፡፡ ከሁሉም በበለጠ የእኛ ፈቃድ ከአባታችን ፈቃድ በኋላ ሊሆን ይገባል (ማቴ. 6፡1ዐ፣ ሉቃስ 22፡24)፡፡ ማንኛውም የፀሎት መዘግየት ተስፋ
ሊያስቆርጠን አይገባም ሁሌ ተስፋ ሳንቆርጥ (ሳናቋርጥ) ልንፀልይ ይገባናል፡፡ (ሉቃስ 18፡1)
ከምንም ያህል ረዥም ጊዜ በፊት ጌታን የተቀበልን ቢሆን እንኳ ጌታ ሆይ ፀሎትን አስተምረኝ የሚለው ትክክለኛ ጥያቄ ነው (ሉቃስ 11፡1)፡፡ በህይወትዎ በየትኛው የፀሎት አቅጣጫ ነው አሁንም በፀጋው ማደግ የሚፈልጉት?
ሐሙስ ነሐሴ 1, 2006 ዓ.ም
በየዕለቱ ለራስህ ሙት
ተጻራሪ በሚመስል ሁኔታ ለራስ በመሞት ብቻ በእውነት እንኖራለን፡፡ በተጠመቅን ጊዜ ለአሮጌው ማንነታችን በመሞት በአዲስ ሕይወት እንደገና እንነሳለን፡፡ በጥምቀት ውኃ በተቀበርን ጊዜ አሮጌዉ የኃጢአቱ ሰውነታችን ለዘለቄታው በሞተ መልካም ነበረ፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ያለፈዉ ልማዳችንና ዝንባሌያችን በውስጣችን እስከ አሁን ያለና በህይወታችን የበላይ ለመሆን ሲጥር የይታያል፡፡ ከጥምቀታችን በኋላ አሮጌው ማንነታችን ደጋግሞ እንድሞት ሊደረግ ይገባል፡፡ ክርስቶስ የክርስትያንን ሕይወት ከመስቀል ጋር ያዛመደው ለዚህ ነው፡፡
ሉቃስ 9፡23-24 ምን ማለቱ ነው?
ብዙዎች መሸከም የሚገባቸው መስቀል ክፉ ህመም፣ አመቺ ያልሆነ የህይወት ውጣ ውረድ ወይም አካለ ስንኩልነት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ከእነዚህ የትኛውም ከባድ ቢሆንም የክርስቶስ ቃላት ትርጉማቸው ከዚህ ያለፈ ነው፡፡ መስቀል መሸከም ማለት እለት በዕለት ራስን መካድ ነው፡፡ አልፎ አልፎም አይደለም የህይወታችን አንዱ ክፍልም አይደለም ነገር ግን ሁለመናችን ሊሆን ይገባል፡፡
የክርስትያን ህይወት የተሰቀለ ህይወት ነው፡፡ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ እኔም አሁን ህያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል (ባለ 2፣2ዐ)፡፡ በጥንቱ ዓለም በመስቀል የሚሠቀሉ ቶሎ አይሞቱም ነበር፡፡ በመስቀል ላይ ለብዙ ሰዓታት አንዳንዴም ለቡዙ ቀናት እንደተሠቀሉ ይሠቃዩ ነበር፡፡ አሮጌው ተፈጥሮአችን በመስቀል ላይ የተሰቀለ ቢሆንም ከመስቀሉ ላይ ለመውረድና በህይወት ለመቆየት ይታገላል፡፡
ራሳችንን መካድ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አሮጌው ተፈጥሮአችን መቆየት እንጂ መሞት ይፈልግም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ ራሳችንን መስቀል አንችልም፡፡ “ማንም ሰው ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት አይችልም፡፡ ማድረግ የምንችለው ክርስቶስ ሥራውን
እንዲያከናውን ከእርሱ ጋር መስማማት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የነፍስ ዝማሬ የሚሆነው ጌታ ሆይ ልቤን እኔ መስጠት ስለማልችል አንተ ውሰደው የሚል ይሆናል፡፡ ልቤ የአንተ ንብረት ነው፡፡ አንተ ራስህ በንፅህና ጠብቀው እኔ ለአንተ ልጠብቅ አልችልም፡፡ እኔን ደካማ ከሆነውና ክርስቶስን ከማይመስለው ማንነቴ አድነኝ፡፡ በነፍሴ ውስጥ የአንተን ንፁህ የሆነውን የፍቅር ፍሰት በሙላት ወደማገኝበት ሰማያዊና ቅዱስ ከባቢ አየር ከፍ አድርገኝ፣ ለውጠኝ እንደገና ቅረጸኝ፡፡
“ይህ ዓይነት ራስን መካድ የሚያስፈልገው በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ህይወት ዓመታት ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ በእያንዳንዱ ወደ ሰማይ በሚደረግ ጉዞ እርምጃ ላይ ሊታደስ ይገባል፡፡ ቀጣይ በሆነ ራስን መካድና በክርስቶስ ላይ በመደገፍ ብቻ በደህንነት መጓዝ እንችላለን፡፡ Ellen .G. white Christ object lesson P.P 159-160፡፡ በየዕለቱ ራስን ለክርስቶስ
ማስረከብ የግድ ያስፈልጋል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ለራስዎ የሞቱት መቼ ነበር? የዛሬውን ጥቅስ በተመለከተ መልስዎ ምን ይነግርዎታል?
ዓርብ ነሐሴ 2, 2006 ዓ.ም
ለተጨማሪ ጥናት፡- Ellen .G. white “ Consecration” ገጽ 43-48 ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ፤ በዘመናት ምኞት ‹‹ኒቆዲሞስ›› በሚለው ርዕስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከራስ ጋር የሚደረግ ትግል እስከ ዛሬ ከተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ በጣም ታላቁ ጦርነት ነው፡፡ ራስን መስጠት ፈቃድን ሁሌ ለእግዚአብሔር አሣልፎ መስጠት ትግልን ይጠይቃል ነገር ግን ነፍስ በቅድስና ልትታደስ ለእግዚአብሔር መሰጠት አለባት፡፡” Ellen G. white ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ፡፡
‹‹ራሳችንን ጠብቀነው በእግዚአብሔር ሙላት እንዲሞላ ማድረግ አንችልም፡፡ ልንሞላ ባዶ ልንሆን ይገባናል፡፡ ለምነን ልቀበል የምንችለው ራስን በማዋረድ የክርስቶስን ልብ፣ አእምሮ፣ መንፈስና ፈቃዱን በመቀበል ብቻ ነው፡፡” ኤሌን ጂ. ኋይት በሰማያው ሥፍራ ገጽ 155
“የእግዚአብሔር መንፈስ ልብን ሲቆጣጠር ህይወትን ይለውጣል፤ ኃጢአተኛ አስተሳሰቦች ይወገዳሉ፤ ክፉ ሥራዎች ይሸነፋሉ፤ ፍቅር፣ ራስን ዝቅ ማድረግና ሠላም፣ የቁጣን፣ የምቀኝነትንና የሀብትን ምኞት ሥፍራ ይወስዳሉ፡፡ የኃዘንን ሥፍራ ደስታ ይወርሳል፡፡ ፊትም የሰማይን ብርሃን ያንፀባርቃል፡፡ ነፍስ በእምነት ራሷን ለእግዚአብሔር ስታስረክብ በረከት ይመጣል፡፡ ይህ ሲሆን ማንም ሰብዓዊ ዓይን የማያየው ኃይል በእግዚአብሔር አምሳል የሆነን አዲስ ማንነት ይፈጥራል፡፡ ኤለን ጂ. ኋይት የዘመናት ምኞት ገጽ 173
የመወያያ ጥያቄዎች፡-
- በክርስቶስ ስለ መጽናት የእርስዎ የግል ተሞክሮ ምንድነው? ከክርስቶስ ጋር ሲገናኙ ምን ይሆናል? እንደሚፈልጉ መልስ ያላገኙባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው እምነትዎን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ውስጥ በአእምሮአችን መያዝ የሚገባን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ምንድናቸው?
- በየቀኑ እንድንክደው የተጠራንበት ራስ ተፈጥሮው ራሱ ምንድነው? እስቲ እንደዚህ እናስብ ራስዎን የማይክዱ ከሆነ ራስዎ አስተሳሰብዎን ወይም ተግባርዎን ቢቆጣጠር ምን ዓይነት ኑሮ ይኖሩ ይሆን? በምን ዓይነት ሁኔታ
ጌታን ማሳየት ይችላል? የዚህ ጥያቄ መልስ ኑሮአችን ከጌታ ስለ መለየት ምን ይነግርዎታል?