ከሐምሌ 19 – 25, 2006ዓ.ም
ሰንበት ከሰዓት
የሚከተሉትን ጥቅሶች ለዚህ ሳምንት ጥናት ያንብቡ፡፡ ሉቃ. 5፣27-32፣13፡1-5፣ ማቴ. 22፡2 -14፣ ዘካ. 3፡1-5 ዮሐ. 8፡30,3፣ ሉቃ. 14፡25-27፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ፡- “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል፡፡ ዮሐ. 3፡14
እ ሥራኤላውያን በምድረበዳ በእባብ በተነደፉ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን የነሐስ እባብ ሠርቶ እንዲሰቅልና የተሠቀለውን የሚያይ ሁሉ እንዲድን መመሪያ ሠጠ፡፡
የነሐስ እባብ ምን ማዳን የሚችሉ ነገሮች አሉት? ምንም የለውም፡፡ መዳን የመጣው ከእግዚአብሔር ብቻ ነበር፡፡ የነሐሱን እባብ (ምስል) በማየት የእሥራኤል ልጆች የደህነታቸው ብቸኛ አማራጭ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ እንደሆነ እምነታቸውን ያሳያሉ፡፡
እግዚአብሔር መንፈሳዊ ትምህርት ሊያስተምራቸው ወደደ፡፡ እርሱ የሞትን ምልክት ወደ ህይወት ምልክት ለወጠው፡፡ የነሐሱ እባብ እኛን ከኃጢአታችን ሊያድነን የኃጢአታችን ተሸካሚ የሆነውን ክርስቶስን ይወክላል፡፡ እኛም በእምነት በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን በመመልከት ገዳይ ከሆነው ከጥንቱ ዘንዶ እንድናለን፡፡
ይህ ካልሆነ ዕድል ፈንታችን በኃጢአት መሞት ነው፡፡ እንደ ሰብዓዊነታችን ኃጢአተኛ በመሆናችን ፀጋ የግድ እንደሚያስፈልገን የእግዚአብሔር ቃል ይገልፃል፡፡ ይህም ፀጋ በክርስቶስ በኩል ተሰጥቶናል፡፡
በዚህ ሳምንት ክርስቶስ ያስተማራቸውን ለመዳናችን የሚሆኑ ቀላል ደረጃዎች እናያቸዋለን፡፡
ለሐምሌ 26 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡
እሁድ ሐምሌ 2ዐ 2006 ዓ.ም
የሚያስፈልግህን እወቅ
ሉቃስ 5፡27-32 ያንብቡ፡፡ እርስዎ በየትኛው ቡድን እንደሆኑ እንዴት ያውቃሉ?
_____________________________________________________
_____________________________________________________
ብዙ ሰዎች አካላዊ ጤንነታቸው ሙሉ ስለሆነ ሐኪም አያስፈልጋቸውም፡፡ እነዚያ ሰዎች ግን በመንፈስ ጤነኛ ናቸው? ከሰው ልጆች ሁሉ “መልካም ያደረገ አንድ እንኳ የለም” (መዝ. 14፡3)፤ “ማናቸውም በራሳቸው አይፀድቁም (ሮማ 3፡1ዐ)፡፡ ለአእምሮአችን ፈቃድ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን ልናደርግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን አናፀድቅም፡፡ ስለዚህ “ፃድቃንን ልጠራ አልመጣሁም (ሉቃስ 5፡32) ሲል ፃድቃን ሳይሆኑ ፃድቃን ነን ይሉ የነበሩ ፈሪሳውያንን ማለቱ ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙ ቢያምኑም እነርሱ ግን መንፈሳዊ እውራን ነበሩ (ዮሐ. 9፡40፣41)፡፡
ስለዚህ ከኃጢአት ለመፈወስ የመጀመሪያው እርምጃ ኃጢአተኝነታችንን ማወቅና ራሳችንን ለመፈወስ የማንችል መሆናችንን መቀበል ነው፡፡ ነገር ግን እውራን ከሆንን የሚያስፈልገንን እንዴት ማየት እንችላለን? እውነተኛ የሆነውን ሁኔታችንን እንዳናውቀው የሚያደርገን ኃጢአት ከሆነ ኃጢአተኞች መሆናችንን እንዴት ልንቀበለው እንችላለን?
_____________________________________________________
_____________________________________________________
አዳኝ በጣም እንደሚያስፈልገን እንድናውቅ አይናችን ሊከፈት የሚችለው እንዴት ነው? ዮሐ. 16፡8ን ተመልከቱ፡፡
ትክክለኛውን መንፈሳዊ ሁኔታችንን ማየት እንድንችል የሚያደርገን የዓይን ኩል መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ከማንኛውም ሥራ አስቀድሞ እርሱ ኃጢአተኞች መሆናችንን ያሳምነናል፡፡ ያለማቋረጥ ከኃጢአታችን ለማምለጥ የማንችልና በደለኞች መሆናችንን በአእምሮአችን እንዲሰማን ያደርጋል ይህም በውስጣችን አዳኝን እንድንናፍቅ ያደርጋል፡፡ ይህን ጥሪ በምንሰማበት ጊዜ ልንታዘዘው ይገባናል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ ሌላ ምንም ነገር ሊደረግልን በማይችል ሁኔታ ልባችን መንፈስ ቅዱስን ላለመስማት ይደነድናል፡፡ እንዴት አስፈሪ ሐሳብ ነው!
የበደለኝነት ስሜት ክፉ ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ ለእርስዎ ጥቅም ይውል ዘንድ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው?
_____________________________________________________
_____________________________________________________
ሰኞ ሐምሌ 21, 2ዐዐ6 ዓ.ም
ንስሐ
ሐጢአታችንን ማወቃችን ብቻውን በቂ አይደለም፤ በንስሐ ሊታጀብ ይገባዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ሦስት ነገሮችን ያጠቃልላል ኃጢአተኛ መሆናችንን መቀበል፤ ስለ ሐጢአቱ ማዘንና ዳግም ያን ኃጢአት ላለማድረግ ፍላጐት ማሳየት፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሚጐድል ከሆነ እውነተኛ ንስሐ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ይሁዳ ኃጢአተኛ መሆኑን የተቀበለ ቢሆንም ጌታውን በመሸጡ ምንም ሃዘን አልተሠማውም (ማቴ. 27፡3፣4) በፀፀት ተጨነቀ እንጂ ንስሐ አልገባም፡፡ የእርሱ ንሰሐ ሚደርስበትን ቅጣት በመፍራት እንጂ ክርስቶስን የመውደድ አልነበረም፡፡
ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት የምናየው መጥምቁ ዮሐንስና ክርስቶስ አገልግሎታቸውን የጀመሩት “ንስሐ ግቡ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና” (ማቴ. 3፡2፣417) በሚለው ስብከት መጀመራቸው እውነት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት የመጀመሪያ የወንጌል ተልዕኮ ጉዞ ያደረጉ ጊዜ ህዝቡ “ንስሐ እንዲገቡ” ሰበኩላቸው (ማቴ. 6፡12)፡፡ ከጴንጤ ቆስጤ ቀን በኋላም ጴጥሮስ ለህዝቡ በተመሳሳይ ሁኔታ ንስሐ እንዲገቡ ሰበከ (ሐዋ. 2፡38፣ 3፡19)
በአጠቃላይ ንስሐ ለመዳን አስፈላጊ እንደሆነ ትኩረት ለመስጠት ክርስቶስ የተናገራቸውን ጠንካራ ቃላት ይመልከቱ፡፡ እዚህ ላይ ምን ዓይነት መልዕክት እየሠጠን ነው፡፡ ሉቃስ 13፡1- 5 ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኛ መሆናቸውን ክርስቶስ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ሰሚዎቹን ንሥሐ ካልገባችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ (ቁ. 5)፡፡ ያለ ንስሐ መዳን አይቻልም ምክንያቱም ንስሐ ከሌለ ሰዎች ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አልሠጡም ማለት ነው፡፡
“የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንደሚመራህ አታውቅምን” ተብሎ ተነግሮናል ይህ ምን ማለት ነው? የበረዶ ግግር ይሰባበራል፤ ነገር ግን እነዚያ ደቃቆቹም ቢሆኑ በረዶ ናቸው፡፡ ያ ተመሳሳዩ የበረዶ ግግር ሙቀት ከሚያመነጭ ነገር አጠገብ ቢቀመጥ ይቀልጣል፡፡ የእኛም የትዕቢታችን በረዶ እንዲቀልጥ ወደሚያሞቀው የእግዚአብሔር ፍቅርና መልካምነት ልንጠጋ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው ፍቅር በምናገኘው ማስረጃ ሁሉ ላይ በምንችለው ያህል ሁሉ መነጋገር እንዴት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
“ንስሐ የምንገባው እግዚአብሔር እንዲወደን አይደለም ነገር ግን እርሱ ንስሐ እንድንገባ ፍቅሩን ስለሚገልጽልን ነው፡፡” Ellen-G white Chirst Object lesson P.189.
የእግዚአብሔር ፍቅር ማረጋገጫዎች ምንድናቸው? በእርሱ መልካምነት እንድትታመን የሚያደርግህ የያዝከው የተለማመድከውና የተማርከው ምን አለህ? እነዚያን ምክንያቶች ሁልጊዜ መነጋገር ለምን ያስፈልጋል? በተለይም በመጥፎ ጊዜያት?
ማክሰኞ ሐምሌ 22 2ዐዐ6 ዓ.ም
በኢየሱስ እመን
እውነተኛ ንስሐ ኢየሱስ ብቸኛው የግል አዳኝ ከመሆኑ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ኢየሱስ የእርሱን በረከት ለመቀበል ማመን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ “ቢቻልህ ትላለህ ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል” (ማር. 9፡23)፡፡ የምንድን እስከሆነ (ለመዳን) እምነት ያስፈልገናል፡፡ ይህንን ስለሚያውቅ ሰይጣን እንዳናምን ሊያደርገን የሚችለውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡ (ሉቃ. 8፡12)፡፡
እንደ የሱስ አነጋገር “ማመን ማለት ምን ማለት ነው? እምነት አንድ ነገር ይሆናል ብሎ ከማሰብ በጣም የሚሠፋ (የሚበልጥ) ነገር ነው፡፡ ከአእምሮ ልምምድም የሚያልፍ ነው፡፡ የሚያድን እምነት ከፍሬ ነገሩ የራቀ (የተለየ) አይደለም፡፡ በተቃራኒው እምነት ተጨባጭ የሆነ ዓላማ አለው፤ ያም ክርስቶስ ነው፡፡ እምነት በአንድ ነገር በተለይም በአንድ ሰው ማመን ብቻ አይደለም፡፡ እምነት የሱስንና ለእኛ ሲል መሞቱን ማመን ነው፡፡ በእየሱስ “ማመን” ማለት እርሱን ማወቅና እርሱ ማን እንደሆነ መረዳት (ዮሐ. 6፡69) እና እርሱን በግል መረዳት ነው (ዮሐ. 1፡12)፡፡
እግዚአብሔር እንዲሁ ዓለምን ወዶ አንድ ልጁን ሰጥቷል፡፡ ይህንን ያደረገው በእውነት በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለምን ህይወት እንዲያገኝ ነው፡፡ ነገር ግን የእርሱ ሞት ሁሉንም ያድናል ማለት አይደለም፡፡ በእርሱ ጽድቅ ልንሸፈን ይገባል፡፡ በእርሱ በማመን ጽድቅ፣ ዋስትና እና በመጨረሻው ቀን ከሞት እንደሚያነሳን ታላቅ ተስፋ ይኖረናል፡፡
ኃጢአተኛ ኑሮን ለኖረች ሴት የሱስ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል . . . እምነትሽ አድኖሻል (ሉቃስ 7፡48,50) በማለት ዋስትና ሰጣት፡፡ ያ ምን ማለት ነው? እምነታችን ያድነናል ማለት ነው? እንደ ወንጌላችን ጌታችን አንዳንድ ሰዎችን ሲፈውስ “እምነትህ ፈውሶሃል (ማቴ. 9፡22፣ ማር. 1ዐ፡52፣ ሉቃስ 17፡19) ብሏቸዋል፡፡ ይህንን ሲል በእነርሱ እምነት ላይ የሚገኝን የተለየ የመፈወስ ኃይልን መመደቡ አይደለም፡፡ የእነርሱ እምነት በክርስቶስ የማዳን ኃይል ላይ ያላቸውን መታመን ማሳያ ነበር፡፡ የእምነት ኃይል የሚመጣው ከግለሰቡ (ከሚያምነው ሰው) ሳይሆን ግለሰቡ ከሚያምነው አምላክ ነው፡፡
በፀሎት ዙሪያ ያለውን የእምነት ሚና በተመለከተ መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድነው? (በተለይም ፈውሰን በሚመለከት) ከላይ ከተሠጡ ቁጥሮች ላይ ፀልየን ፈውስ ያልተገኘ
እንደሆነ የእምነትን ጉድለት ያሳያል የሚለው ድምዳሜ ስህተት የሚሆነው ለምንድነው፡፡
ረቡዕ ሐምሌ 23 2ዐዐ6 ዓ.ም
የሠርጉ ልብስ
ክርስቶስ በህዝቡ ፊት በመቀመጥ የሚያስደነግጥ ነገር ነገራቸው፤ ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከጻፎች ካልበለጠ በቀር ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም አላቸው” ማቴ. 5፡2ዐ፡፡ በህጉ ላይ የተፃፈውን በጥንቃቄ በመጠበቅ ከፈሪሳውያን የሚሻሉ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የሆነ ሆኖ እነርሱ የወደቁት ባህሪያቸው ሰውን ለማስደነቅ ለመማረክ እንጂ እግዚአብሔርን ለመማረክ አልነበረም፡፡ እንደዚህ እንዳንሆን የሱስ አስጠንቅቆናል ማቴ. 6፡1
ማቴ. 22፡2-14 ያንብቡ፡፡ ንጉሡ ሁሉም ሰው የሰርጉን ልብስ መልበሱን እርግጠኛ መሆን የፈለገው ለምንድነው? ልብሱ የሚያሳየው (የሚወክለው) ምንድነው? ኢሳ. 61፡1ዐ፣ ዘካ. 3፡1-5 ይመልከቱ፡፡
___________________________________________________________
____________________________________________________________
ንጉሡ የሠርጉን ልብስ የሰጠው በነፃ ነው፡፡ እዚያ ስፍራ የተገኙ እድምተኞች የመጡት ከመንገድ ላይ እየሄዱ ካሉበት በመሆኑ ለሠርግ የሚሆን ያሸበረቀ ልብስ ወይም ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ የላቸው ይሆናል፡፡ ጥሪው ግብዣውም ሆነ የሠርጉ ልብስ የንጉሡ ሥጦታዎች ናቸው፡፡ በሠርጉ ለመገኘት የሚያስፈልግ የነበረው ሁለቱንም ሥጦታዎች መቀበል ብቻ ነው፡፡
ከኤደን ውድቀት ጀምሮ፤ እያንዳንዱ ሰው መንፈሳዊ እርቃኑን ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በኃጢአት ከወደቁ በኋላ ራቁትነታቸው ስለተሰማቸው የማይመቸውንና ራቁትነታቸውን ሊሸፍን ብቁ ያልሆነውን የበለስ ቅጠል ሠፍተው ለመልበስ ሞከሩ (ዘፍ. 3፡7)፤ የሰው ልጅ ሊኖረው የሚችለው ጽድቅ “እንደ መርገም ጨርቅ ነው” ኢሳ. 64፡6፡፡
ልክ ታሪኩ ላይ እንደተመለከትነው የሚያስፈልገንን ልብስ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፡፡ እርሱ ለአዳምና ለሄዋን ልብስ ሠርቶ አልብሷቸዋል (ዘፍ. 3፡21) ይህን ያደረገው ኃጢአተኛን እንደሚሸፍነው የራሱ ጽድቅ ምሳሌ በማድረግ ነበር፡፡ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተክርስትያኑ “ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ይሠጣታል”፣ “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር” (ራዕይ 19፡8፣ ኤፌ. 5፡27)የለም፡፡ ይሄ ልብስ በእምነት እርሱን የግል አዳኛቸው አድርገው ለተቀበሉ ሁሉ የሚሠጥ ምንም እድፈት የሌለበት የክርስቶስ ባህሪይና የራሱ ጽድቅ ነው፡፡ Ellen G.white Christ object lesson P.310
ከሁሉ ነገር በላይ መዳናችን የሚመጣው ክርስቶስ እንደ ሥጦታ ከሚሠጠን መሸፈኛ ላይ ብቻ መሆኑን የምናስተውለውና የምናምነው ለምንድ ነው? ሁሌ ይህንን ማስታወስ ለምን ያስፈልጋል?
__________________________________________________________
__________________________________________________________
ሐሙስ ሐምሌ 24 2006 ዓ.ም
ኢየሱስን ተከተለው
በእምነት ስንሆን የሚያስፈልገንን እናውቃለን፣ ንስሐ እንገባለን፣ ኃጢአታችንን እንናዘዛለን እናም የክርስቶስን ፅድቅ እንደራሳችን በመቀበል ደቀመዝሙር እንሆናለን፡፡ በምድራዊ አገልግሎቱ ዘመን ክርስቶስ እንደ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የመሳሰሉትን ደቀመዛሙርቱ እንዲሆኑ ጠርቷቸዋል፡፡ ያም ጥሪ ያላቸውን ሁሉ እንዲተውና እርሱን እንዲከተሉ የሚፈልግ ነበር (ማቴ. 4፡2ዐ፣22 ፣ ማር. 1ዐ፡28፣ ሉቃስ 5፡28)፡፡ በእርግጥም መከተል በሚለው ድርጊት ገላጭ ቃል “ደቀመዛሙርቱ” እንዲሆኑ ጠርቷቸዋል፡፡
የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለመሆን የሚያስፈልጉ ሁለት ነገሮች ምንድናቸው? ዮሐ. 8፡3ዐ,
13 ይመልከቱ፡፡
አንዳንድ ሰዎች እምነትንና በክርስቶስ ትምህርቶች ማመንን የመጀመሪያው ከሁለተኛው የሚበልጥ በማድረግ ሊለያዩት ይሞክራሉ፡፡ ኢየሱስ ግን እንደዚህ ዓይነት ልዩነት አላደረገም፡፡ ለእርሱ ትክክለኛ ደቀመዝሙር ለመሆን ሁለቱም ነገሮች እርስ በእርስ የሚዛመዱና መሠረታዊ ናቸው፡፡ የክርስቶስ ደቀመዛሙር ለክርስቶስ ለራሱና ለቃሉ ህይወቱን የሠጠ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በትምህርቶቹ በመመሰጥ የእምነትን መልክ ብቻ በመያዝ ክርስቶስን ራሱን ያለማየት አደጋ ይታያል፡፡ መርሳት የሌለብን ነገር ደግሞ ከክርስቶስ ጋር ባለን ጉዞ የሚያስፈልገን እምነት ብቻ ነው ብሎ ከማሰብ አደጋ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
የክርስቶስ ደቀመዝሙር መሆን የሚያስከፍለው ከፍተኛ ዋጋ ምንድነው? ሉቃስ 14፡25- 27ን ተመልከቱ፡፡
ክርስቶስ “መጥላት” የሚለውን ቃል “ጥቂት መውደድ” የሚለውን ለማጋነን ተጠቀመበት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል የሚገኘው ተመሳሳዩ ንባብ የክርስቶስን ቃላት ግልጽ ያደርገዋል “እናቱን ወይም አባቱን ከእኔ በላይ የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይችልም” (ማቴ. 1ዐ፡37)፡፡ ደቀመዝሙርት ለመሆን ከፈለግን ክርስቶስ በህይወታችን የመጀመሪያውን ሥፍራ ሊወስድ ይገባል፡፡
ክርስቶስን መከተልና፣ የእርሱ ደቀመዝሙር መሆን የሚያስከፍለው ዋጋ ምንድነው? ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ጉዞህ ለዚህ ምን ምላሽ ይሠጣል?
__________________________________________________________
__________________________________________________________
ዓርብ ሐምሌ 25, 2006 ዓ.ም
ለተጨማሪ ጥናት፡- ኤሌን ጂ. ኋይት፣ “ንስሐ” ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ ገጽ 23-32 “የክርስቶስ መንፈስ አስተሳሰባችንን ካልቀሰቀሰ በቀር ንስሐ ልንገባም ሆነ ይቅርታ ከኢየሱስ ልናገኝ አንችልም፡፡ Ellen G-white p. 26”
“በቀራኒዮ መስቀል ላይ የተሰቀለውን በግ በምናይበት ጊዜ፣ የመዳን ሚስጥር ግልጽ ሲሆንልን የእግዚአብሔር መልካምነት ወደ ንስሐ ይመራናል፡፡ ለኃጢአተኞች በመሞት ክርስቶስ የማይገመተውን ፍቅሩን አሳየን፤ ኃጢአተኛው ይህንን ፍቅር ሲያስተውል፤ ልቡ ይለሰልሳል፣ አእምሮው ይነካል እናም በነፍሱ ውስጥ ፀፀትን ይቀሰቅሳል፡፡” ገጽ 26-27
“ራሱን ዝቅ የሚያደርግና የተሠበረ ልብ ለእውነተኛ ንስሐ የተሸነፈ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ምንነትና የቀራንዮን ዋጋ በአድናቆት ያያል፤ እንደ ልጅም ለሚወደው አባቱ ኃጢአቱን ይናዘዛል፣ ስለዚህ በእውነት የተፀፀተ ሰው ኃጢአቱን ሁሉ ወደ ክርስቶስ ያመጣል፡፡ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከአመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ፃድቅ ነው” (1ኛ ዮሐ. 1፡9) ተብሎ ተጽፏል፡፡
የመወያያ ጥያቄዎች፡-
- ብዙዎች የበደለኝነት ስሜታቸውን በአልኮል፣ በእፆች፣ በአለማዊ ደስታና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ዕብደት ለመርሳት ይሞክራሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች አንዱም የማይሠራው ለምንድነው? በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለን አንድ ሰው ከበደለኝነት እውነተኛ የሆነ መፍትሔ እንዲያገኝ እንዴት ሊረዱት ይችላሉ?
- የእውነተኛ ንስሐን ፍሬ ሳናፈራ ኃጢአታችንን ግን ማየት እንችላለን፡፡ ይህ ዓይነቱ እውነተኛ ንስሐ የማይሆነው ለምንድነው? የንስሐ ፍሬ ጥቅሙ ምንድነው? ከእግዚአብሔር ተቀባይነትን ለማግኘት የሚሠሩ መልካም ሥራዎች ናቸውን? መልስዎትን ያብራሩ፡፡
- የክርስቶስ ጽድቅ ነፃ ሆኖም ግን እርካሽ አለመሆኑን ያስቡ፡፡ ምንም እንኳን እኛ ባንከፍልም እግዚአብሔር በመስቀል ላይ ታላቅ ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ ኃጢአታችን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነና ምን ያህል የወደቅን መሆናችንን እናስብ፤ እኛ እንድን ዘንድ የእግዚአብሔርን ልጅ መሞት እስኪያስፈልገው ድረስ የኃጢአታችንን ክፋት መጠን ምን ያህል አንደሆነ ያስቡ፡፡