ሐምሌ 12-18, 2006 ዓ.ም
ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ጥናት፡- ሉቃ. 18፡9-14 ዮሐ. 6፡44፣ ሉቃ. 15፡3-10 ማቴ. 2ዐ፡28፣ ዮሐ. 8፡34-36፣ ዮሐ. 6፡35፡ 47-51 ያንብቡ፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ፡- “እግዚአብሔር እንዲሁ አለምን ወድዋልና አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጠፋ የዘላለም ህይወት ትሆንለት ዘንድ እንጂ”፡፡ (ዮሐ. 3፡16)
ብ ዙውን ጊዜ “ሞት የህይወት ክፍል ናት እንላለን” አይደለም ሞት የህይወት ተቃራኒ እንጂ የህይወት ክፍል አይደለችም፡፡ ከእውነተኛ ማንነቱ በተቃራኒው በመጥራት ሞትን ያለ ሥፍራው እናስቀምጣለን፡፡ ሆኖም ምንነቱን ብንረዳም፤ ያለ መለኮታዊ ኃይል እርዳታ የሁላችንም ዕጣ ፈንታ ሞት መሆኑን እርግጠኞች ነን፡፡
ታድለናል! የሚያስፈልገው እርዳታ መጥቷል፡፡ እግዚአብሔር፣ ወሰን በሌለው ፍቅሩ መዳንን በኢየሱስ በኩል ሠጥቶናል፡፡ መልአኩ የመሲሁን መወለድ ባወጀ ጊዜ ስሙን “የሱስ” (በእብራውያን ቃል ትርጓሜውም አዳኝ) እርሱ ህዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል፡፡” (ማቴ. 1፡21)፡፡
በዚህ ሳምንት የየሱስን የማዳን ሥራ እናጤናለን፡፡ በመጀመሪያ ትኩረታችን የሚሆነው
የድነታችን መሠረት ላይ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ በውጤቱ ላይ ይሆናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ነው፡፡ ኃጢአታችንን በተመለከተ ሁለት አማራጮች አሉን፤ የኃጢአታችንን ዋጋ በገሃነም የእሳት ባህር እንከፍላለን ወይም ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ የከፈለውን ዋጋ እንቀበላለን፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የሰጠንን የርህራሄ ሥጦታ ስንከልስ እስቲ እንደገና በትህትና ክርስቶስ የግል አዳኛችን በመሆኑ ላይ ያለንን እምነት እንፈትሽ፡፡
ለሐምሌ 19 ሰንበት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡
እሁድ ሐምሌ 13, 2006 ዓ.ም
ድነት ከእግዚአብሔር የሆነ ሥጦታ ነው
በዮሐ. 3፡16 ሁለት ግሦች እግዚአብሔር ለእኛ ድነት ያደረገውን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህ ግሦች እርስ በእርስ የሚጣጣሙት እንዴት ነው? የመዳናችንን ጅምር (መሠረት) በተመለከተ ምን ይገልፁልናል?
በእንግሊዝኛው ወደደ፣ በተለይም ዛሬ በተለምዶ ጥቅም ላይ እንደሚውለው ዓይነት፣ በግሪኩ (aga pao) “ለመውደድ” የሚለው ቃል የሚሠጠውን ብቸኛ የሆነ መሰል የሌለውን ፍቅር ለመግለጽ የሚጠቅመውን በፍጹም ሊወክል አይችልም፡፡ በአዲስ ኪዳን ይህ ቃልና የዚህ ተመሳሳይ ስም አጋፔ (agape) “ፍቅር የሚለው እግዚአብሔር ለማይገባቸው ፍጥረታቱ ያሳየውን ጥልቅና የማያቋርጥ ፍቅር ያሳያል፡፡”
ፍቅር የእግዚአብሔር የላቀ የባህሪዩ መግለጫ ነው፡፡ እርሱ እኛን ይወደናል ብቻ ሳይሆን ራሱ ፍቅር ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡8)
የእግዚአብሔር ፍቅር በስሜቱ ላይ ወይም ቅድሚያ የሚሠጣቸው ነገሮች ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ፍቅሩ አንዱን ከሌላው የሚለይ ወይም በሥራችን ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን በሙሉ የሰውን ፍጥረት በሙሉ እርሱን የማይወዱትን ጭምር ይወዳል፡፡
እውነተኛ ፍቅር በሚያደርጋቸው ድርጊቶች ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደ ሰው ሌሎችን እንደምንወድ እንናገራለን፡፡ ነገር ግን ድርጊቶቻችን ተቃራኒውን ያመለክታሉ፡፡ (1ኛ ዮሐ. 3፡17, 18) እንዲህ አይነት በእግዚአብሔር ዘንድ የለም፡፡ ፍቅሩ በድርጊቱ ይገለፃል፡፡ ከዚህ ፍቅር የተነሳ ለድነታችን አንድያ ልጁን ሰጠን ይህንን በማድረግ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ሰጠን፣ ይኸውም ራሱን ሰጠን፡፡
ሉቃስ 18፡9-14 ያንብቡ፡፡ ይህ ታሪክ የእኛ አመለካከት የእግዚአብሔርን ፀጋውን በተመለከተ ምን መሆን እንደሚገባው ነው የሚያስተምረን? ምናልባት የየሱስን ፍርድ ሳናደንቀው ይህንን ታሪክ ብዙ ጊዜ አንብበነው ሊሆን ይችላል እላችኋለሁ ከዚህ ይልቅ ይህ ሰው (ቀራጩ) ፃዲቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ (ሉቃስ 18፡14) ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፍርድ ሲያውጅ የሰሙ ተደንቀው ይሆናል፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊነት አይደለም?
______________________________________________________________
______________________________________________________________
አዎ ይህ በፍጹም ለእርሱ የተገባው አይደለም፡፡ ድነት ማለት እንደዚያ ነው፡፡ ድነት የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፡፡ ሥጦታዎች ክፍያዎች ወይም ሠርተን ያገኘናቸው አይደሉም ዝም ተብሎ የሚወሰዱ ናቸው መዳንን ዝም ብለን እንወስዳለን እንጂ አንገዛውም፡፡ ምንም እንኳን ፀጋ የሚለውን ክርስቶስ የተጠቀመው በጣም በጥቂቱ ቢሆንም ድነት በፀጋ እንደሆነና ፀጋም ላልተገባው የሚሠጥ እንደሆነ በግልጽ አስተምሯል፡፡
እግዚአብሔር የሚገባዎትን ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ለምን?
______________________________________________________________
______________________________________________________________
ሰኞ ሐምሌ 14 2ዐ13 ዓ.ም
ድነት ከእግዚአብሔር ሀሳብ የመነጨ
ቀላል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ መዳናችን ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ለእኛ የዋለው ውለታ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው እኛ ጋብዘነው ሳይሆን አባት ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ ላከው፡፡ የዚህ ሃሳብ አመንጭ አባት መሆኑን ክርስቶስ በተለያየ ጊዜ “የላከኝ እርሱ” እና “የላከኝ አባቴ” በማለት አረጋግጧል፡፡ ዮሐ. 7፡28፣ 8፡29፣ 12፡49ን ያንብቡ፡፡
እንደ ማቴ. 6፡44 አባት ለድነታችን ሌላ ምን አድርጓል?
ኃጢአተኞች መሆናችንና እግዚአብሔርን አለመውደዳችን ተጨባጩ እውነታ እንደሆነ እርሱ ግን ወዶን የኃጢአታችንን ይቅርታ እንድናገኝ በልጁ በኩል መንገድን አዘጋጀልን፡፡ (1ኛ ዮሐ. 4፡1ዐ) ወደ እርሱ የሚስበን ይህ አስደናቂ ፍቅሩ ነው፡፡
አባት ብቻ ሳይሆን ልጅም በድነታችን ጉዳይ ንቁ ሚና ተጫውቷል፡፡ እርሱም ተጨባጭ ተልዕኮ ይዞ ወደ ምድር መጣ፡፡ “የሰው ልጅ የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን መጣ” (ሉቃስ 19፡10) በማንኛውም ጊዜ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስላለው ስለእርሱ ስናሰላስል ወደ ራሱ ይስበናል (ዮሐ. 12፡32)
እግዚአብሔር እኛን ለማዳን በሚያደርገው ጥረት ምን ያህል ርቀት ለመሄድ ፈቃደኛ ነው? ሉቃስ 15፡3-10ን ተመልከቱ፡፡
እነዚህ ሁለት መንትያ ምሳሌዎች የሚያሳዮን እግዚአብሔር እኛ ወደ እርሱ እንድንሄድ ዝም ብሎ የተቀመጠ ሳይሆን በትጋት እኛን መፈለጉን ነው፡፡ የሚፈልገን እግዚአብሔር አለን፡፡ እጅግ አደገኛ በሆኑ ሩቅ ሥፍራዎች እንኳን ብንቅበዘበዝ ወይም መኖሪያ ብናጣ፤ እንኳ ምንም አይደለም እስኪያገኘን ድረስ ሳይደክም የሚፈልገን ጌታ አለን፡፡
እረኛው ከመንጋው መካከል አንድ በግ እንደጠፋ ያዝናል ይጨነቃል፡፡ መንጋውን ደጋግሞ ይቆጥራል፡፡ ከመንጋው አንድ በግ መጥፋቱን እርግጠኛ ሲሆን እንቅልፉን አይተኛም፡፡ዘጠና ዘጠኙንም በበረት ትቶ የጠፋውን ፍለጋ ይሄዳል፡፡ ቀኑ ሲጨልም ውዥምብሩ ሲበዛ፣ መንገዱ እጅግ አስቸጋሪ ሲሆን፣ የእረኛው ጭንቀት እጅግ ይጨምርና በፍለጋውም እጅግ ይተጋል፡፡ የጠፋውን አንዱን በግ ለማግኘት የሚችለውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡
“የደመ-ነፍስ ጩኸቱን በሩቅ ሲሰማ ምን ያህል ደስ ይለው ይሆን ድምፁን ተከትሎ ዳገቱን ይወጣል እስከ ገደሉ አፋፍ ድረስ ህይወቱን በአደጋ ጥሎ ፍለጋ ይሄዳል፡፡ የድረሱልኝ ድምፁ በጉ ለሞት የተቃረበ መሆኑን ስለሚነግረው ፍለጋው ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ጥረቱ ሁሉ ተሳክቶለት የጠፋው ተገኘ፡፡ Ellen. G. white Christ Object Lesson P.P 188::
ማክሰኞ ሐምሌ 15, 2006
አስፈላጊ የሆነው ሞት (ለኃጢአት)
መጥምቁ ዮሐንስ ስለ የሱስ ሲናገር “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29) በማለት ገልጾታል፡፡ ይህ እይታ በቅዱሳት መፃህፍት ተዘግቦ የተቀመጠን ታሪክ ለሚያነብና በቤተመቅደስ የሚቀርብ የነበረውን መስዋዕት ለሚያውቅ እሥራኤላዊ ለማስተዋል እጅግ ቀላል ነበር፡፡ አብረሃም “ለሚቃጠል መስዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል፡፡” በማለት እምነቱን ሲገልጽ እውነትም በይስሐቅ ፈንታ የሚቀርበውን የመስዋዕት በግ እግዚአብሔር አዘጋጀ፡፡ (ዘፍ. 22፡8,13)፡፡ እሥራኤላዊውን በግብፅ ከኃጢአት ባርነት በመለኮታዊ ኃይል የመውጣታቸው ምልክት ይሆን ዘንድ ጠቦት አርደዋል፡፡ (ዘፀ. 12፡ 1-13)፡፡ የቤተመቅደስ አገልግሎት ከተቋቋመ በኋላም በቀን ሁለት ጠቦቶች ጧትና ማታ ይታረዱ ነበር፡፡ (ዘፀ. 29፡38,39) እነዚህ ሁሉ ሊመጣ የነበረው የመሲሁ ምሳሌ ነበሩ፡፡ “እንደ በግ ወደ ሞት ተነዳ” ምክንያቱም “እግዚአብሔር የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳ. 53፡6,7)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እየሱስን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ሲያስተዋውቅ” ዮሐ. 1፡29 የክርስቶስን ከኃጢአት የሚዋጀውን ውክልና ሞት እያስተዋወቀ ነበር፡፡
ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎት ጊዜ፣ ደቀመዛሙርት ለምን መሞት እንዳለበት ማስተዋል ቢያቅታቸው ስለ ሞቱ ደጋግሞ ተናግራዋል (ማቴ. 16፡22)፡፡ የሱስ ቀስ በቀስ የሞቱን ዓላማ ገልጿል፡፡ ክርስቶስ እርሱ በእኛ ምትክ መሞቱን ለማሳየት ምን ዓይነት ምሳሌ ተጠቅሟል? ማቴ. 2ዐ፡28፣ ዮሐ. 1ዐ፡11ን ይመልከቱ፡፡
“ነፍሱን ለወዳጆቹ አሳለፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለም (ዮሐ. 15፡13)፡፡ እነርሱ ባያስተውሉትም መስዋዕትነቱን ባይቀበሉትም እንኳን ይህ እውነት ሆኖ ፀንቶ ይኖራል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሷል “ለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ ይሆን ዘንድ” ማቴ. 26፡28
ክርስቶስ የሞተው በፈቃዱ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አባት ብቸኛ (አንድያ) ልጁን እንደሠጠ እንዲሁ ልጁ ደግሞ የሰብዓዊውን ዘር ለማዳን ህይወቱን ሰጠ፡፡ ይህንን ለማድረግ ማንም አላስገደደውም፡፡ “እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም” (ዮሐ. 1ዐ፡18)
ክርስቶስን በግልጽ የተቃወመውና እንዲገድለው ለጲላጦስ አሣልፎ የሠጠው ቀያፋ እንኳን ሳይወድ የክርስቶስ ሞት የምትክ ሞት መሆኑን መስክሯል፡፡ (ዮሐ. 11፡49-51)፡፡
እስቲ የሰው ልጆች እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ስለሰጣቸው ነገር ምን ያህል ውለታ ቢሶች ስለመሆናቸው ያስቡ፡፡ በዚህ ዓይነት ወጥመድ ለለመግባትዎ በምን እርግጠኛ ይሆናሉ? በተለይም በአንዳንድ አስቸጋሪ በሆኑ ነገሮች ውስጥ ሲያልፉ እንደዚህ ውለታ መርሳት ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?
______________________________________________________________
______________________________________________________________
ረቡዕ ሐምሌ 16, 2006 ዓ.ም
ከኃጢአት ነፃ
ያለ ክርስቶስ፤ የኃጢአትና ክፉ የሆነው የወደቀው ሰብዓዊ ዘር ምኞት ባሪያዎች ነን፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር በመኖር ፈንታ ራሳችን ደስ ባሰኘን ሁኔታ ኖረናል፡፡ ሊወገድ የማይችለው የዚህ ባርነት ውጤት ሞት ነው፣ ምክንያቱም የኃጢአት ዋጋ ሞት ስለሆነ፡፡
ነገር ግን ክርስቶስ “ለምርኮኞች ነፃነትን “ለተጨቆኑት መፈታትን ሊያውጅ መጣ” (ሉቃስ 4፡18)፡፡ እነዚህ የጦር ምርኮኞች ሳይሆኑ በመንፈሳቸው የሰይጣን እሥረኞች ናቸው (ማር. 5፡1-20፣ ሉቃስ 8፡12)፡፡ ጌታችን የሱስ መጥምቁ ዮሐንስን ከሄሮድስ እሥር ቤት ነፃ አላወጣውም ነገር ግን እርሱ በኃጢአተኛ ህይወታቸው ሰንሠለት የታሰሩትንና ከበደለኝነት ስሜት ከባድ ሸክም እና የዘላለም ፍርድ ኃጢአተኞችን ነፃ አወጣ፡፡
በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው ታላቅ ተስፋ ምንድ ነው? ዮሐ. 8፡34-36 ይመልከቱ በቁጥር 36 “በእውነት የሚለው ቃል ትክክለኛ ያልሆነ የሰውን ዘር እንደ ሠንሠለት ሆኖ እጅና እግርን የሚያስር የውሸት አርነት ደግሞ መኖሩን ያስታውቃል፡፡ የኢየሱስ ሰሚዎች የነበሩ ሁሉ አብርሃም የነፃነታቸው ተስፋ መሆኑን የሚያምኑ ነበሩ፡፡ እኛም ተመሳሳዩን አደገኛ ነገር እያደረግን ነው፡፡
ሰይጣን እኛን በማንኛውም ነገር ላይ ለምሳሌ በቅዱስ መጻህፍት ዕውቀት፣ በግል መልካምነታችን እና ከክርስቶስ ውጭ ለመዳናችን እንዳገለገልን በሚቆጠሩ ሥራዎቻችን ላይ እንድንታመን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ምንም ያህል አስፈላጊዎች ቢሆኑም አንዳቸውም እንኳን ከኃጢአታችንና ከሚያመጣብን ኩነኔ ነፃ ሊያደርጉን አይችሉም፡፡ ብቸኛው እውነተኛ ነፃነት የኃጢአት ባሪያ ሆኖ በማያውቀው በልጁ ብቻ ነው፡፡
እየሱስ ኃጢአትን ይቅር በማለት ደስ ይለዋል፡፡ አራት ሰዎች ሽባውን ሰው ወደ እርሱ ባመጡ ጊዜ ይህ ሰው የታመመው በሚኖረው ወራዳ (የተልከሰከሰ) ህይወት ምክንያት መሆኑን ቢያውቅም ንስሐ መግባቱንም ያውቅ ነበር፡፡ ፈውስን በሚለምኑ በዚህ ሰው ዓይኖች ውስጥ ክርስቶስ ይቅርታን ለማግኘት በልቡ ያለውን ጉጉትና ለመዳን ብቸኛው መፍትሄ ጌታ እንደሆነ ያለውን እምነት አየ፡፡ የሱስም ሰውየውን በፍቅር፣ “ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል” አለው (ማር. 2፡5)፡፡ እነዚህ ቃላት ሰውየው እስከዚያ ቀን ድረስ ከስማቸው ሁሉ እጅግ ጣፋጭ ነበሩ፡፡ የተስፋ መቁረጥ ሸክም ከአእምሮው ተወግዶ ከይቅርታ የሚገኘው ነፃነት መንፈሱን ሞላው፡፡ በክርስቶስ መንፈሳዊና አካላዊ ፈውስ እናገኛለን፡፡
በፈሪሳዊው ቤት ኃጢአተኛዋ ሴት የክርስቶስን እግሮች በእምባዋ አጥባ ሽቶ ቀባች (ሉቃስ 7፡37፣38)፡፡ ኢየሱስ ፈሪሳዊው ድርጊቱ አግባብ ያልሆነ አድርጐ መቁጠሩን ስላወቀ እንዲህ ሲል አብራራው (ብዙ ኃጢአቷ ይቅር ተብሎላታል (ሉቃስ 7፡47) ከዚያም ለእርሷ ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል (ሉቃስ 7፡48) አላት፡፡
ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” የሚሉ ቃላት በየትኛውም ጊዜ ከምንሰማቸው ቃላት የተሻሉ የሚሆኑት ለምንድነው?
______________________________________________________________
______________________________________________________________
ሐሙስ ሐምሌ 17, 2006
ክርስቶስ የዘላለም ህይወት ይሠጠናል
በኃጢአታችን ምክንያት ሞት ይገባናል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የእኛ የነበረውን የኃጢአትን ቅጣት በፋንታችን ተቀበለ፡፡ እርሱ ምንም ያልበደለ ሆኖ ሳለ በደላችንን ወሰደና ቅጣታችንን ተቀብሎ እኛ ኃጢአተኞች ስንሆን ያልበደልን እንድንባል አደረገ፡፡ መጥፋት ሲገባን በእርሱ የዘለዓለምን ህይወት አገኘን፡፡ ዮሐ. 3፡15 ይህንን አስገራሚ ተስፋ ይሠጠናል፡፡ በእርሱ የሚያምን ማንም እንዳይጠፋ የዘለዓለምን ህይወት እንዲያገኝ ይህ ተስፋ በዮሐ. 3፡16 መጨረሻ ላይ በድጋሚ ተሰጥቷል፡፡
አንዳንዶች ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው ከተቀበሉ በኋላ እንኳን የዘለዓለም ህይወት ተስፋ እውነት የሚሆነው ከክርስቶስ ዳግም ምፃት በኋላ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን የድህነት ተስፋ የሚገለፀው በአሁኑ ጊዜ ነው፡፡ “ማንም በልጁ የሚያምን የዘላለም ህይወት አለው” (ዮሐ. 3፡36)፡፡ “በየሱስ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት አለው” አሁን “ወደ ፍርድ አይመጣም” “በመጨረሻም ከሞት ወደ ህይወት ተሻግሯል”፡፡
(ዮሐ. 5፡24)፡፡ ስለዚህ ብንሞትና በመቃብር ብንተኛ እንኳን፣ ይህ ጊዜያዊ ዕረፍት ከዘለዓለም ህይወት እውነተኛነት ሊያርቀን አይችልም፡፡
የሱስ አዳኛችን ሲሆን ህይወታችን ሙሉ ትርጉም ይኖራታል፣ በተሟላ ኑሮ እንደሰታለን፡፡ የሱስ እንዲህ ብሏል “እኔ የመጣሁት ህይወት እንዲሆንላችሁና እንዲበዛላችሁ ነው” (ዮሐ. 1ዐ፡1ዐ)፡፡ እውነተኛ እርካታን ሊሰጠን በማይችለውና ጊዚያዊ መሸጋገሪያ ከሚሆን የዚህ ዓለም ደስታ ፋንታ በፍጹም የተለየ በሆነ መንገድ በእርሱ ዘንድ ያለን የማያባራ (የማያልቅ) እርካታን ይሠጠናል፡፡ ይህ አዲስ የተሟላ ኑሮ ሁሉ ነገራችንን ያጠቃልላል፡፡ ክርስቶስ አካላዊ ጤንነትን የሚያድሱ ብዙ ተዓምራቶችን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ከኃጢአት የነፃና የታደሰ መንፈሳዊ ህይወት በእርሱ ላይ እምነት ያለውና የመዳንን እርግጠኛነት የሚያምን ህይወት ሊሰጥ ፈለገ፡፡
ክርስቶስ እርሱን የመቀበልን ውጤት ለመግለጽ ምን ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቀመ? በተግባራዊው የየዕለት ህይወታችን ይህ ምን ማለት ነው? ዮሐ. 6፡35፣ 47-51 ተመልከቱ፡፡ ስለ ዘለዓለም ህይወት አሰላስሉ፡፡ የማይጠፋ ህይወት ብቻ አይደለም፣ ከሁሉም በላይ የተባረከ፣ የሚያረካ እና ከእግዚአብሔር በፍቅር ህብረት በአዲስ ምድር በደስታ መኖር ነው፡፡ ምንም እንኳን እስከአሁን የምንኖረው በዚህች ምድር ቢሆንም በከፊል እንኳ የዘለዓለም ህይወት ምን እንደሆነ አውቀን መደሰት የምንጀምረው እንዴት ነው?
ዓርብ ሐምሌ 18, 2ዐዐ6 ዓ.ም
ለተጨማሪ ጥናት፡- አሌን ጂ. ኋይት ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ዱካ “የኃጢአተኛው እግዚአብሔርን መፈለግ” ገጽ 17-22፣ በሰለክትድ ሜሴጅስ፣ በ1883 የተሰጠው መልዕክት “ገጽ 350-354 አንደኛ መጽሐፍ፡፡
“በመስቀል ላይ የተሰቀለውን አዳኝ ስንመለከት በሰማያዊ ታላቅነትና ኃይል የተፈጸመውን መስዋዕትነት ትርጉሙንና መጠኑን በሙላት እንረዳለን፡፡ የድህነት ዕቅድ በፊታችን ከብሯል፤ የጐልጐታው ሀሳብ አኗኗራችንን ያነቃዋል የተቀደሰ ፍላጐት በውስጣችን ይጨምራል፡፡ በልባችንና በከንፈራችን ለእግዚአብሔር ምሥጋናን ይጨምራል፤ የጐልጐታን ሁኔታ ሁልጊዜ በአእምሮው የሚያድስ ህይወት ኩራትና ራስን ማምለክ በውስጡ አያድጉም፡፡
የአዳኙን ተወዳዳሪ የሌለውን ፍቅር የሚይዝ በሐሳቡ ከፍ ያለ ይሆናል፣ ልቡ ይነፃል ባህሪዩም ይለወጣል፡፡ የዓለም ብርሃን ለመሆንና የእግዚአብሔርን ባህሪይና አስደናቂ ፍቅሩን ለማንፀባረቅ ወደ ፊት ይሄዳል፡፡ የክርስቶስን መስቀል የበለጠ ስናሰላስል “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበትን እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበትን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” ያለውን የሐዋሪያው ጰውሎስን አነጋገር በሙላት እናስተውላለን (ገላ. 6፡14) አሌን ጂ. ኋይት የዘመናት ምኞት 661
የመወያያ ጥያቄዎች፡-
- ድነት ሥጦታ ነው ማለትም ነፃ ነው፡፡ ቢሆንም ምንም ዋጋ አያስከፍልም? ይህን ነፃ ሥጦታ ለመቀበል የሚያስከፍለው ዋጋ ምንድነው?
- በሰኞ ቀን ትምህርታችን ድነት ምንጩ እግዚአብሔር እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ እርሱ እኛን ለማዳን ሁሉንም ጥረት ያደርጋል፡፡ ሆኖም ክርስቶስ ሲናገር የእግዚአብሔርን መንግሥትና ድጽቁን እንድንሻ ነግሮናል (ማቴ. 6፡33)፡፡ “በጠባቧ በር ለመግባት ጣሩ (ሉቃስ 13፡24) የሚሉ የእርሱ ቃላት መዳናችንን መፈለግ እንዳለብን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህንን እንዴት እንገልጸዋለን፡፡
- የክርስቶስ መስቀል ሞት የእግዚአብሔርን ቅን ፍርድ የሚያሳየው እንዴት ነው? የእግዚአብሔርንስ ምህረት የሚየሳየው እንዴት ነው?
- በራሳችን መልካም ሥራ ወይም በራሳችን ኃይል ትዕዛዛትን በመጠበቅ መዳናችንን በራሳችን የምንፈጽመው ቢሆን ይህ ምን ያህል የኃጢአትን መጥፎነት ሊነግረን ይችል ይሆን? የክርስቶስ ሞት ብቻ ሊዋጅ መቻሉ የኃጢአትን መጥፎነት እንዴት ሊያሳየን እንደሚችል አስቡበት፡፡
- ኃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶች በሰንበት ውስጥ የዘላለም ህይወት ምን እንደሚመስል ቅድመ-ቅምሻ አይተዋል፡፡ የዘላለም ህይወት በሰንበት ይመሰላል የሚለው ሀሳብ ጥሩ ስሜት ሊፈጥርልን የሚችለው በምን መንገድ ነው?