3ኛ ትምህርት: መንፈስ ቅዱስ

EAQ314_03

ሐምሌ 5-11, 2006 ዓ.ም

ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ጥናት ዮሐ. 14፡16-18፣ 14፡26፣ 15፡26፣ ማቴ. 12፡31,32፣ ዮሐ. 16፡8፣ ዮሐ. 3፡5-8፣ ሉቃ. 11፡9-13

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፡፡” (ዮሐ. 14፡16)

ከ ሦስቱም የእግዚአብሔር አካላት በጣም በትንሹ የተስተዋለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ወደ እኛ እጅግ የቀረበዉን፣ አዲስ ትውልድን በእኛ የሚፈጥረውን በእኛም ዘንድ የሚኖረዉንና እኛንም የሚለውጠውን አካል እርሱን የምናውቀው በጣም በጥቂቱ እንደሆነ መናገር ራሱ ምፀታዊ አባባል ነው፡፡

ለመጀመር ያህል የዚህ ምክንያቱ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ለአባትም ሆነ ለልጅ ከሚሰጠው መግለጫ መንፈስቅዱስን የገለጸው አነስተኛ በሆነ መልኩ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ማጣቀሻዎች ቢኖሩም ብዙዎቹ ዘይቤያዊ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ብዙ ነገር የሚነግረን ቢሆንም አፈጣጠሩን በተመለከተ ግን እጅግ ጥቂት ነው፡፡

የሌላኛው ምክንያት መነሻ የሚሆነው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው፡፡ እርሱ (መንፈስ ቅዱስ) የሁላችንንም ትኩረት ወደ ራሱ ሳይሆን ወደ ክርስቶስ እንዲሆን ለማድረግ ይጥራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በመዳናችን ዕቅድ ውስጥ አብንና ወልድን በማገዝ ሠርቷል ይህ ማለት ግን እርሱ የበታች ነው የሚያሰኝ አይደለም፡፡

በዚህ ሳምንት ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያስተማረውን ስንሰማ የሚለውጠው የእርሱ መገኘት በመካከላችን በህይወታችን እንዲሆን እንፀልይ፡፡

ለሐምሌ 12 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡

እሁድ ሐምሌ 6, 2006 ዓ.ም

የክርስቶስ ተወካይ

ክርስቶስ አይቀሬ የሆነ ሞቱን ሲነግራቸው ደቀመዛሙርት በፍርሃትና በኃዘን አደመጡት፡፡ እርሱ በተለያቸው ጊዜ አስተማሪ፣ መካሪ እና ጓደኛ የሚሆናቸው ማን ነው? የሚያሳዝነውን ፍላጐታቸውን በማወቅ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር የሚሆን ምትክ ሊልክላቸው ቃል ገባ፡፡

ክርስቶስ ለምትኩ ምን የተለየ ስም ነበር የተጠቀመው? ዮሐ. 14፡14-18 ይመልከቱ፡፡ ይሄ ስም ለመንፈስ ቅዱስ በትክክል የሚገጥመው በምን መልኩ ነው? ዮሐ. 14፡26 ደግሞ ይመልከቱ፡፡

ረዳት፣ መካር አጽናኝ የሚሉት (Parakletos) ፖራክላጦስ ለሚለው ለግሪኩ ቃል የተሰጡ ትርጓሜዎች ናቸው፡፡ ይህም ቃል “ፖራ” በአጠገብ ወይም በጐን ከሚለውና “ቅላጦስ” ከሚለው ገላጭ ቃል ትርጓሜውም “የተጠራ” ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ነው፡፡ ግልጽ የሆነው ትርጉሙም “ሊደግፍ የተጠራ” ይህም “እገዛ ለመስጠት የተጠራ አካል” የሚል ሃሳብ ይሰጣል፡፡ አማላጅ ረዳት፣ መካሪ ወይም ህጋዊ ጠበቃ ማለትም ይሆናል፡፡

ጰራቅሊጦስ የሚለውን አገላለጽ በአዲስ ኪዳን የተጠቀመው ዮሐንስ ብቻ ነው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ይህንን አገለላለጽ ለክርስቶስ ተጠቅሞታል (ዮሐ. 2፡1) በምድር ሳለ ጌታችን የደቀመዛሙርቱ መካሪ ረዳትና አጽናኝ ነበር፡፡ ስለዚህ የእርሱ ምትክ
የሆነው የእርሱን ስም መውሰዱ ተገቢነት አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልጅ ጠይቆ በአባት የተላከ ነበር፡፡ (ዮሐ. 14፡16-20) መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ የክርስቶስን ሥራ ይቀጥላል፡፡

በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ደቀመዛሙርቱ የክርስቶስን መገኘት ተለማምደው ነበር፡፡ “አባት እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡” (ዮሐ. 14፣18) ክርስቶስ “እኔ በእናንተ ውስጥ” ሲል (ዮሐ. 14፡2ዐ) አንዳንድ ጊዜ መጥቶ እንደሚጐበኛቸው ሳይሆን በዘላቂነት በቀረበ ወዳጅነትና ቅርበት ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን መናገሩ ነበር፡፡
በእርግጥ የክርስቶስ ሰብዓዊ ሥጋ መልበሱ በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት እንዳይችል አድርጐት ነበር፡፡ በተቃራኒው መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ሥፍራ ይገኝ ነበር፡፡ (መዝ. 139፡7) በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ክርስቶስ በየትኛውም ሩቅ ሥፍራ ለሚገኙ ሁሉ ያለ ምንም መከልከል ይደርሳል፡፡
ምንም እንኳን የመንፈስ ቅዱስን አሠራርና ባህርዩን መረዳት ቀላል ባይሆንም የእርሱን እውነተኛነት የተለማመዱት በምን መንገድ ነው?

ሰኞ ሐምሌ 7, 2ዐዐ6 ዓ.ም

መንፈስ ቅዱስ አካል ነው

ኤሌን ጂ. ኋይት እንዲህ ጽፋለች፡- “የመንፈስ ቅዱስ ተፈጥሮ ምሥጢር ነው እግዚአብሔር ስላልገለጸው ሰዎች መግለጫ ሊሠጡ አይችሉም፡፡ ይህን በመሰሉ የሰብዓዊ አእምሮ ሊያስተውላቸው ከባድ በሆኑ ምሥጢሮች ዝምታ መልካም ነው፡፡” (Acts of the apostels,pg 52)

ምንም እንኳን “መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን ብናረጋግጥም ከመንፈሳችን ጋር በመሆን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይመሰክርልናል፡፡ መለኮታዊ አካል ባይሆን ኖሮ በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ የተሠወረውን ሚስጢር ሊመረምር አይችልም ነበር፡፡” Ellen white evangelism, pp 616,617. ይህ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን (ሮሜ 8፡6 እና 1ኛ ቆሮ. 2፡1ዐ,11) በሰብዓዊ ተፈጥሮአችን ምክንያት ውስኖች ብንሆንም በቅዱሳት መጻህፍት አማካይነት መንፈስ ቅዱስ አካልና እንዲሁም እርሱ መለኮታዊ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ክርስቶስ ስለመንፈስ ቅዱስ የተናገረው ይህን ድምዳሜ ይደግፋል፡፡

መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን የሚያሳዩ የትኞቹ ድርጊቶች ናቸው? ዮሐ. 14፡26፣ 1526፡7-14ን ይመልከቱ፡፡
መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን የሚያመላክቱ የተለያዩ ድርጊቶችን እንደሚፈጽም ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ እርሱ ማንኛውም ሰው/አካል ከሚያስተምረን በላይ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክር (ዮሐ. 15፡26) ክርስቶስ የተናገራቸውን ነገሮች ሁሉ እንድናስታውስ
የሚያደርግ (ዮሐ. 14፡26)፣ በዓለም ይፈርዳል (ዮሐ. 16፡8)፣ ይናገራል ይሰማል እናም ወደ እውነት ሁሉ ይመራል (ዮሐ. 16፡13) እናም የሚያስተውል ማንነት (አካል) በመሆኑ ክርስቶስን ያከብራል (ዮሐ. 16፡14)፡፡
የክርስቶስን ትምህርት ተከትሎ የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች መንፈስ ቅዱስ የአካል ባህሪያት እንዳሉት በግልጽ ጽፈዋል፡፡ ፈቃድ ያለው ለመሆኑ (1ኛ ቆሮ. 12፡11)፣ እውቀት (ሐዋ. 15፡28፣ ሮሜ 8፡27)፣ እና ስሜት ያለው ለመሆኑ (ሮሜ 15፡3ዐ፣ ኤፌ. 4፡3ዐ)

መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አካል በመሆኑ ራሳችንን በትህትና ለእርሱ ምሪትና ፈቃድ አሣልፈን እንሠጣለን፡፡ በልባችን ውስጥ እንዲኖርም እንጋብዘዋለን (ሮሜ 8፡9)፣ ህይወታችንን እንዲለውጥ (ቲቶ 3፡5)፣ እናም በባህሪያችን ውሰጥ የመንፈስ ፍሬዎችን
እንድናፈራ (ገላ. 5፡22, 23)::
እኛ ለብቻችን ረዳተ-ቢሶች ነን፤ ክርስቶስ እንደገባልን የተስፋ ቃል ሆነን የምንገኘው በውስጣችን በሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደማንኛውም ሌሎች ሥጦታዎች ሁሉ ሥጦታ በመሆኑ እምቢ ሊባል ይችላል፡፡ እርስዎ በየዕለቱ መንፈስ ቅዱስ እንዲያደርጉ ከሚፈልገው ፈቀቅ አለማለትዎን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

________________________________________________________________
________________________________________________________________

ማክሰኞ ሐምሌ 8, 2006 ዓ.ም

መንፈስ ቅዱስ መለኮት ነው

ጌታ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ለደቀመዛሙርቱ ሲያስተዋውቅ “ሌላኛው” ረዳት በማለት ጠርቶታል (ዮሐ. 14፡16)፡፡ ክርስቶስ “ሌላኛው” ለሚለው የተጠቀመው የግሪኩ ቃል “Allos” (አሎስ) ይህም “Hetro” (ሄትሮስ) የተለያየ ዓይነት ሆኖ ሌላኛው ለሚለው ቃል ተቃራኒ የሆነ ሲሆን ትርጓሜውም ከተመሳሳይ ዓይነቶች አንዱ ወይም ሌላኛው ማለት ነው፡፡ አባትንና ልጅን ያስተሳሰረው ተመሳሳይ ባህሪይ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ግንኙነትም ውስጥ በግልጽ ታይቷል፡፡
ክርስቶስ “መንፈስ ቅዱስ ሊመጣ ስላለው ነገር ይነግራችኋል” ብሏል፡፡ (ዮሐ. 16፡13) ወደፊት ሊሆን ያለውን ሊነግረን የሚችል መለኮታዊ አካል ብቻ ነው (ኢሳ. 46፡9,10) የመንፈስ ቅዱስ መለኮትነት ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲጽፉ ሰዎችን በመምራት ተግባሩ ተመስክሯል፡፡ እርሱም (ጌታችን) “ዳዊት ራሱ በመንፈስ በመመራት” ማር. 12፡36 (በመዝ. 110፡1) ተጽፎ የሚገኘውን ተናግሯል እያለ ሊያስገነዝባቸው ጥሯል፡፡

ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ያለማቋረጥ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ተቀብሏል፡፡ በጥምቀቱ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ (ማቴ. 3፡16፣17) “በመንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረበዳ ተመርቷል” ሉቃ. 4፡1፡፡ በፈታኙም ላይ ድልን በመቀዳጀት “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመልሷል” (ሉቃ. 4፡14)፡፡ እርሱ ያደረጋቸው ድንቆች በሙሉ የተከናወኑት በመንፈስ ቅዱስ ነበር (ማቴ. 3፡16, 17) ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የመደገፉ እውነታ ሌላኛው የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊነት የሚያሳይ መግለጫ ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ከመለኮት በሚያንስ በሌላ ነገር ላይ
ይደገፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡
የመንፈስ ቅዱስ ሠፋ ያለው የመለኮትነት ማስረጃ የሚሆነው የሚገኘው ደግሞ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እኩል መሆናቸውን በሚናገሩ ጥቅሶች ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ አዳዲስ ደቀመዛሙርትን እንዲያጠምቁ ለሐዋሪያቱ በሰጠው ኃላፊነት “በአብ
በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” (ማቴ. 28፡19) እንዲያጠምቁ ነገራቸው፡፡

የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት ለመረዳት የሚቀጥሉት ጥቅሶች እንዴት ይረዱናል? ማቴ. 12፡31, 32

________________________________________________________________
________________________________________________________________

ክርስቶስን በመቃወም እና መንፈስ ቅዱስን ተቃውሞ በመናገር መካከል ስላለው ልዩነት ሲገልጽ የሰው ልጅ ላይ የሚቃወም ይቅር ሊባል እንደሚችል ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን ይቅርታን የማያገኝ እንደሆነ መናገሩ መንፈስ ቅዱስ ተራ አካል አለመሆኑን ያመለክታል፡፡ የእግዚአብሔርን ስም በክፉ ማንሳት (መሳደብ) በእግዚአብሔር በራሱ ላይ በቀጥታ የሚደረግ ኃጢአት ነው፡፡ ከዚሀ የተነሳ መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ስላሴዎች አንዱ አካል ነው ወደሚለው ማጠቃለያ እንደርሳለን፡፡ ምንም እንኳን ይቅር ስለማይባሉ ኃጢአቶች ብዙ የተፃፈ ቢሆንም፤ ፊት ለፊት የሚገኘው የንባቡ አውድ እንደሚያሳየን ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸውን ያደነደኑ እርሱ ለመዳናችን የሠራውን ሥራ እነርሱ የዲያብሎስ (የክፉ መንፈስ) ነው ይላሉ፡፡

ረቡዕ ሐምሌ 9, 2006 ዓ.ም

የመንፈስ ቅዱስ ሥራ

ሥጋን በለበሰው በክርስቶስና ቅዱሳት መጻህፍት ላይ ያለውን የመንፈስ ቅዱስን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚና ቀደም ሲል ጠቅሰናል፡፡ አሁን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በመዳናችን ላይ ያለውን ሚና እንመልከት፡፡

እኛ አዳኙን እንድንቀበለው ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ምን አስፈላጊ የሆነ ሥራ ይሠራል?ዮሐ. 16፡8ን ይመልከቱ፡፡

ህመምተኛ መሆኑን አምኖ ሳይቀበል መድኃኒት የሚወስድ አለን? በተመሳሳይ መልኩ እኛ ኃጢአተኛ መሆናችንን ካልተገነዘብን በቀር መዳን አንችልም፡፡ ለስለስ ባለ ነገር ግን በማያቋርጥ ጉትጐታ መንፈስ ቅዱስ ኃጢአት እንደሠራን፣ በደለኞች እንደሆንን እና ፍትሐዊ በሆነው የእግዚአብሔር ፍርድ ፊት መሆናችንን ይነግረናል፡፡

ከዚያም መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ ይመራናል፣ (ዮሐ. 15፡26) የሚያድነን እርሱ ብቻ መሆኑን ይመሰክርልናል፡፡ ክርስቶስ እውነት በመሆኑ (ዮሐ. 14፡6) መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ ሲመራን ወደ እውነት ሁሉ ይወስደናል” (ዮሐ. 16፡13) በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስም የተጠራው በሌላ ስም ሳይሆን “የእውነት መንፈስ” ነው የተባለው፡፡ (ዮሐ. 14፡17)
ኃጢአተኞች መሆናችንን ስናረጋግጥ (ይህም ከኃጢአታችን ንስሐ መግባትን ያስከትላል) ወደ ክርስቶስና ወደ እውነት ስንመራ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ታላቁን ሥራ እንዲሠራ ዝግጁ እንሆናለን፡፡

ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ በጣም ወሳኝ የሚሆነው ለምንድነው? ዮሐ. 3፡5-8ን ተመልከቱ፡፡

ህይወታቸውን በራሳቸው ለመለወጥ ጥረት ያደረጉ ሁሉ ልፋታቸው ምን ያህል ፍሬ ቢስ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ያለ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የዘቀጠውን (የተበላሸውን) ኃጢአት የሞላበት ማንነታችንን አዲስ ለማድረግ በፍጹም አንችልም፡፡ የአንድ ኃጢአተኛ ሰው አዲስ መፈጠር አዲስ የሚፈጥርን የመለኮት ኃይል፤ ያም መንፈስ ቅዱስን ይፈልጋል፡፡ እኛ የዳንነው “በመንፈስ ቅዱስ ታጥበን አዲስ ፍጥረት በመሆን ነው” (ቲቶ 3፡5) መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው አሮጌ ነገር ማደስ (ማሻሻል) ሳይሆን ባህርይን መለወጥና አዲስ ህይወትን መፍጠር ነው፡፡ የነዚህ ዓይነት ተዓምራቶች በግልጽ የሚታዩ በመሆናቸው ማንም ተከራክሮ
ሊያሸንፋቸው በማይችል ሁኔታ ለወንጌል ይሟገታሉ፡፡

መንፈስ ቅዱስ በክርስትና ህይወታችን ጅምር ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሌ በቀጣይነት ያስፈልገናል፡፡ መንፈሳዊ ህይወታችንን ለማሳደግ ያስተምርና ጌታችን ያስተማረውን ደግሞ ያሳስበናል (ዮሐ. 14፡26)፡፡ ብንፈቅድለት ለዘላለም ከእኛ ጋር ሆኖ አጽናኝ ረዳት መካሪ ይሆናል፡፡ (ዮሐ. 14፡፡16)፡፡

መጥፎ ባህሪያት ለማስወገድ ይከብዳሉ አይደለም? ትተናቸው እንኳን ቀጣይ በሆነ መልኩ ጥንቃቄ ካላደረግን መልሰው ያሸንፉናል፡፡ ኃጢአተኛ የሆነው የተፈጥሮ ድካማችንና ዝንባሌአችን ስለ መንፈስ ቅዱስ የማያቋርጥ አስፈላጊነት ምን ይነግረናል?

________________________________________________________________
________________________________________________________________

ሐሙስ ሐምሌ 1ዐ, 2006 ዓ.ም

በመንፈስ ቅዱስ መሞላት

መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆን ማወቅ እንደሚያስፈልገን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ይህ እውቀት ህይወታችንን በሙሉ እርሱ ገብቶ እንዲሞላን መንገድ የማይከፍት ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊውን እንግዳ በየዕለት ህይወታችን ከእኛ ጋር እንዲሆን የማንጋብዘው ከሆነ፣ ባዶ በሆነ ህይወት ውስጥ ገብቶ መንፈሳዊ ባዶነትን ለመፍጠር የተዘጋጀ ሌላ መንፈስ መኖሩን በግልጽ አስተምሯል (ማቴ. 12፡43-45) እየሱስ ራሱ “በመንፈስ ተሞልቶ ነበር” (ሉቃ. 4፡1) ጌታችን ዕለት በዕለት አዲስ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ቅባት ይቀበል ነበር” ኤሌን ጂ. ኋይት Christ object lesson P 139 መንፈስ ቅዱስን ስለምንቀበልበት ሁኔታ ሉቃ. 11፡9-13 ምን ይነግረናል? እነዚህ ቁጥሮች አባታችን መንፈስ ቅዱስን ሊሰጠን ያለውን ፈቃደኝነት እንዴት ያሳዩናል?

በመጨረሻው ዕራት ላይ ጌታችን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ገብቷል፡፡ እነርሱ በጊዜው ስለሚያስፈልጋቸው የመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነትና አጽናኝነት ትኩረት ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ሁኔታው ተለውጦ ደቀመዛሙርቱን ሌላ ግድድሮሽ አገኛቸው፡፡

ከትንሣኤው በኋላ ክርስቶስ የሠጠው የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ትኩረት ምን ላይ ነበር? ሐዋ. 1፡4–8 ተመልከቱ፡፡ ሐዋ. 1፡5 ጌታችን “በመንፈስ ቅዱስ ስለ መጠመቅ” የተናገረውን ብቸኛ ዘገባ ይዟል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን የተለየ ጥምቀት አውጇል፡፡

ማቴ. 3፡11፣ ዮሐ. 1፡33 ነገር ግን ክርስቶስ ወደ ሰማይ እስኪያርግ መጠበቅ ነበረበት፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማለት ምን ማለት ነው?
___________________________________________________________________________________________________

በሐዋ. 1፡8 ክርስቶስ ራሱ ይህንን በተመሳሳይ ዓይነት ገልጾታል፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቃችኋል” (ሐዋ. 1፡5) “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ (ሐዋ. 1፡8)፡፡ መጠመቅ ማለት በአንድ ነገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጥለቅ ማለት ነው በተለይም በውኃ ውስጥ ይህም ሙሉ ማንነትን ያጠቃልላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማለት ሙሉ በሙሉ የመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ ሥር መሆን፣ “በመንፈስ ቅዱስ መሞላት” (ኤፌ. 5፡18)፡፡ ይህ ማለት “አንድ ጊዜ ለዘላለም” ማለት ሳይሆን በተከታታይ መታደስ የሚያስፈልገው ልምምድ ነው፡፡

አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ያውቃሉ ወይ ብሎ ቢጠይቅዎት ምን ምላሽ ይሠጣሉ፡፡ ለምን?

________________________________________________________________
________________________________________________________________

ዓርብ ሐምሌ 11, 2006 ዓ.ም

ለተጨማሪ ጥናት፡- አሌን ጂ. ኋይት “ቃል የተገባለት ኃይል” ገጽ 19-23፣ “የቤተክርስትያን ምክሮች 8ኛ ጥራዝ፣ “የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ” ገጽ 47-56፣ የሐዋሪያት ሥራ”

“በሁሉም ጊዜና ቦታ በማንኛውም ኃዘንና ጭንቀት፣ የሚታየው ነገር ሁሉ ጨለማ ቢመስልም መጪው ጊዜ ግራ የሚያገባ ቢሆን፣ ብቸኝነት ሲሰማንና ረዳት የሌለን ሲመስለን አጽናኙ መንፈስ የእምነት ፀሎት መልስ ሆኖ ይላክልናል፡፡ ሁኔታዎች ከማናቸውም የምድራዊ ጓደኞቻችን ሊለዩን ይችላሉ፤ ነገር ግን ማንኛውም ሁኔታ፣ የትኛውም ርቀት፣ ከሰማያዊው አጽናኝ ሊለየን አይችልም፡፡ የትም ብንሆን የትም ብንሄድ ሊደግፈን ሊያፅናናን ደስ ሊያሰኘን እርሱ ሁሌ በቀኛችን ነው፡፡” ኤሌን ጂ. ኋይት የዘመናት ምኞት 669-670 “መንፈስ ቅዱስ ለህዝቡ ደስታን (ሐሴትን) ከአባት ለመጠየቅ ከሁሉም እጅግ ከፍ ያለ
ሥጦታ ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ የሚሠጠው እንደገና የሚሠራ ኃይል ሲሆን ያለ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ መስዋዕትነት ዋጋ አልነበረውም፡፡ የክፉው ኃይል ለዘመናት ራሱን እያጠናከረ ቆይቷል እናም ሰዎችም ለዚህ ሰይጣናዊ ምርኮ ራሳቸውን ማስረከባቸው እጅግ ያስደንቃል፡፡ ኃጢአት ሊሸነፍ የሚችለው በዚህ ታላቅና ኃይለኛ በሆነው የስላሴ ሦስተኛ አካል እርሱም ኃይልን አድሶ ሳይሆን በመለከታዊ ኃይሉ ሙላት ወደ እኛ በሚመጣው ነው፡፡” በዓለሙ መድኀን የተሠራውን ዋጋ ያለው እንዲሆን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡” ገጽ 671

የመወያያ ጥያቄዎች፡-

  1. ራስን ከፍ የማድረጉ ሰብዓዊ ዝንባሌ እንዳለ ሆኖ፣ የመንፈስ ቅዱስ ራስን ዝቅ ማድረግና ለሌላ ረዳት ሆኖ መሥራቱ ለእኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል?
  2. ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ንግግር ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ከነፋስ ጋር አነፃፅሮታል ከዚሀ ንፅፅር ምን መንፈሳዊ ትምህርት እንማራለን?
  3. አንዳንድ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ማስረጃው “በልሳን መናገር ነው ይላሉ ለዚህ የእኛ ምላሽ ምንድነው?
  4. የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ግላዊ ወይም አንድ ለአንድ እንደሆነ እናስባለን ይህም እውነት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ቤተክርስትያን በህብረት የመንፈስ ቅዱስን መገኘት የምንለማመደው እንዴት ነው?

Copyright © 2013 Ethio SDA . All Rights Reserved