ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ማቴ. 7፡9-1፣ ዮሐ. 14፤ 8-10 ሉቃ. 15፡11-24 ማቴ. 6፡25፣ 9፡14፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ፡- “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ እንዲሁም ነን፡፡” ዮሐ. 3፡1
የሱስ እግዚአብሔርን አባት ብሎ በመናገሩ ደስ ተሠኝቷል፡፡ ወንጌሎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ለእግዚአብሔር አባት የሚለውን ቃል ከ13ዐ ጊዜ በላይ ተጠቅሟል፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ደግሞ ገላጭ ቃላትን በመጨመር “ሰማያዊ አባት” (ማቴ. 6፡14) `ህያው አባት` (ዮሐ. 17፡25) “ቅዱስ አባት” (ዮሐ. 17፡25) በማለት ገልጿል፡፡ ስሞቹም እኛን ከአባታችን ጋር በአንድ የሚያስተሳስረንን ሠንሠለት የሚገልፁ ናቸው፡፡
በተለምዶ፣ አባት ማለት ፍቅር፣ መከላከያ፣ ጠበቃ የሚደግፍ (የሚያኖር) እናም የቤተሰብ ማንነት መገለጫ ነው፡፡ አባት ለቤተሰቦቹ ስም በመስጠት በአንድ ላይ ሰብስቦ ያኖራቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን ሰማያዊ አባታችን እንደሆነ ስንቀበለው እነዚህን ሁሉ መብቶች እንቋደሳለን፡፡
ምንም እንኳን አባትን ማወቅ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ዋና ዓላማችን የቃላትና የአእምሮ ዕውቀት ብቻ እንዲኖረን አይደለም፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው ማወቅ ማለት ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር የቀረበ የግል ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው፡፡
በዚህ ሳምንት ክርስቶስ ስለ አባቱና ወሰን ስለሌለው ፍቅሩ ያስተማረውን እንመረምራለን፡፡ በተጨማሪም የአባትን የልጅንና የመንፈስ ቅዱስን የቅርብ ግንኙነት እናያለን፡፡ ለሰኔ 28 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡
እሁድ ሰኔ 22, 2006 ዓ.ም
በሰማይ ያለህ አባታችን
አባት የሚለው ስም ለእግዚአብሔር አዲስ ስም አይደለም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ብሉይ ኪዳን አባት በሚል ጽፎታል፡፡
(ኢሳ. 63፡16)፣ 64፡8፣ ኤር. 3፡4፣ 19 መዝ. 1ዐ3፡13) ነገር ግን ይህ ስም በብዛት መጠሪያ የሆነው አይደለም፡፡ ለእሥራኤላውያን የግል መጠሪያ ሆኖ ያገለገለው ያህዌህ የሚል ሲሆን በብሉይ ኪዳን ከስድስት ሺህ ስምንት መቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ እየሱስ የመጣው ከያህዌህ የተለየ አምላክን ለማሳየት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእርሱ ተልዕኮ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ስለ ራሱ የገለጸውን መፈጸም ነበር፡፡ ይህንን ለመፈጸም እግዚአብሔርን እንደ ሰማያዊ አባታችን ገለጸው፡፡
የሱስ “በሰማይ” ያለውን አባት ግልጽ አደረገው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያለን አመለካከት ትክክለኛ እንዲሆን ይህንን እውነት ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ የልጆቹ ፍላጐት (መሻት) ግድ የሚለው አፍቃሪ አባት አለን፡፡ ይህ ሲሆን ስለ እኛ ግድ የሚለው አምላክ በዓለማት ሁሉ ብቻውን ታላቅ ቅዱስና ሁሉን ቻይ በመሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ቅዱሳን መላእክት እየሰገዱለት በሰማይ የሚኖር መሆኑን እናውቃለን፡፡ በእርግጥም እርሱ በልጅነት ድፍረት በፊቱ እንድንቀርብ የሚጋብዘን አባታችን ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በሰማይ የመኖሩ እውነት ወደር የለሽ በመሆኑ በአክብሮት ልናመልከው እንደሚገባን ያስታውሰናል፡፡ እነዚህን ሁለቱን አመለካከቶች አንዱን ከሌላው ለይቶ ትኩረት መስጠት ስለ እግዚአብሔር ያለንን ግንዛቤ የተዛባ ስለሚያደርገው በዕለታዊ የህይወት ጉዞአችን ላይ ከፍተኛ ኪሳራን ያመጣል፡፡
ማቴ. 7፡9-11ን ያንብቡ፡፡ የሥጋ አባት ሰማያዊውን አባት እንዴት ሊያንፀባርቅ እንደሚችል ምን ይነግረናል?
እያንዳንዱ ሰው አፍቃሪና የሚጠነቀቅ ወላጅ የለውም በተለያዩ ምክንያቶች አንዳንዶች አባታቸውን እንኳን አያውቁም ስለዚህ ለእነርሱ እግዚአብሔርን ሰማያዊ አባት ብሎ መጥራት የሚሠጣቸው ትርጉም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዳችን ጥሩ የሆነ ምድራዊ አባት ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በተጨማሪ የመልካም አባትን ባህሪያት የሚያንፀባርቁ አንዳንድ ሰዎችን እናውቃቸው ይሆናል፡፡
ሰብዓዊ አባቶች ከፍፅምና የራቁ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ችግሮች እንኳን ቢኖሩብንም ልጆቻችንን እንደምንወዳቸውና የተሻለውን ለእነርሱ ለማድረግ እንደምንጥር እናውቃለን፡፡ ታዲያ ሰማያዊው አባታችን ለእኛ ምን ሊያደርግልን እንደሚችል አስቡ ለአንተ በግልህ እግዚአብሔርን ሰማያዊ አባት ስትለው ምን ትርጉም ይሠጥሃል?
__________________________________________________________
___________________________________________________________
ሰኞ ሰኔ 23, 2ዐዐ6 ዓ.ም
በልጁ የተገለፀ
ዮሐንስ ስለ አባት ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡ “ማንም እግዚአብሔርን አላየውም” (ዮሐ. 1፡18) ከአዳምና ከሄዋን ውድቀት ወዲህ ኃጢአት እግዚአብሔርን ከማወቅ አግዶናል፡፡ ሙሴ እግዚአብሔርን ማየት ፈልጐ ነበር፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ገለፀለት፤ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለው” (ዘፀ. 33፡1ዐ) ከምንም በላይ ቅድሚያ ልንሠጠው የሚገባን ነገር እግዚአብሔርን ለማወቅ መሆን አለበት ምክንያቱም አባትን ማወቅ የዘላለም ህይወት ነውና፡፡ (ዮሐ. 17፡3)
በተለየ ሁኔታ ስለ እግዚአብሔር ልናውቀው የሚገባን ነገር ምንድነው? ኤር. 9፡23-24ን ይመልከቱ፡፡ እነዚህን ነገሮች ማወቅ ለእኛ ለምን አስፈለገ?
_____________________________________________________________
______________________________________________________________
በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ የሠይጣን ዋነኛው የጥቃት ኢላማ የሆነው የእግዚአብሔር ባህሪይ ነው፡፡ ዲያቢሎስ የተቻለውን ሁሉ አድርጐ እያንዳንዱን ሰው እግዚአብሔር ራስ ወዳድ፣ አምባገነን፣ እና ጨካኝ ነው በማለት ማሳመን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ክስ ለመግጠም የተሻለ የሆነው ዘዴ በዚህ ምድር ላይ ክሱ ውሸት መሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ በህይወት መኖር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው በብዙዎች ዘንድ ስለ እግዚአብሔር የነበረውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከልና የእርሱን ተፈጥሮና ባህርዩን ለሰዎች ለማሳየት ነው፡፡ “በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፡18)
ዮሐ. 14፡8-10 ያንብቡ፡፡ ደቀመዛሙርቱ ከክርስቶስ ጋር ከሦስት ዓመት በላይ ከተቀመጡ በኋላ ስለ አባት የሚያውቁት ምን ያህል በጥቂቱ መሆኑን አስተውሉ፡፡ ከእነርሱ አለማስተዋል እኛ ለራሳችን ምን እንማራለን?
_____________________________________________________________
______________________________________________________________
የፊልጶስን ጥያቄ በመስማቱ ኢየሱስ አዝኖና ተደንቆ ነበር፡፡ የተረጋጋ ግሳጼውም ማስተዋል ላቃተው ደቀመዝሙሩ ትዕግሥት የሞላው የፍቅሩ መግለጫ ነበር፡፡ የክርስቶስ መልስ እንዲህ የሚል ይመስላል “ከእኔ ጋር ከተራመዱ በኋላ፣ ቃሌን ሰምቶ፣ ህዝቦችን የመገብሁትን ተዓምራት፣ የበሽተኞችን መፈወስና የሙታንን መነሳት ካያችሁ በኋላ እኔን አታውቁም ማለት ነው? አባቴን በእኔ አማካይነት በሠራቸው ሥራዎች ለማወቅ አልቻላችሁም ማለት ነው?
ደቀመዛሙርቱ አባትን (እግዚአብሔርን) በክርስቶስ በኩል ለማወቅ አቃታቸው ማለት ክርስቶስ አባትን በትክክለኛው ማንነቱ አላሳየውም ማለት አይደለም፡፡ በተቃራኒው ክርስቶስ የአባቱን ማንነት የመግለጹን ተልዕኮ ከእርሱ በፊት ባልታየ ሁኔታ በሙላት ማሳየቱን እርግጠኛ ነበር፡፡ ስለዚህም ለደቀ-መዛሙርቱ እንዲህ ለማለት ቻለ “እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁት ነበር . . . እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ. 14፡7፣9)
ማክሰኞ ሰኔ 24, 2006 ዓ.ም
የሰማዮ አባታችን ፍቅር
የሱስ ክርስቶስ የመጣው ቀደም ሲል በብሉይ ኪዳን የተረጋገጠውን ተወዳዳሪ የሌለውን የአባትን ፍቅር የበለጠ ለማጉላት ነበር፡፡ (ኤር. 31፡3፣ መዝ. 1ዐ3፡13)
“የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅርን ሰጠን!” (1ዮሐ 3፡1) ዓለማትን ሁሉ የሚገዛው ሁሉን ቻይ አምላክ፣ እኛን የማንረባ ደሃ ኃጢአተኞች በብዙ ሚሊዮን ጋላክሲዎች መካከል በምትገኝ ትንሽ ደቃቅ ምድር የምንኖር አባት ብለን እንድንጠራው መፍቀዱ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ይህንን ያደረገው ስለሚወደን ነው፡፡
አባት ፍቅሩን ለመግለጽ ምን የበለጠና ከፍ ያለ ማረጋገጫ ነው የሰጠን ዮሐ. 3፡16,17ን እዩ፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በምሥማር የተቸነከረው በአባት ልብ ውስጥ የሰብዓዊ ዘርን ፍቅር ለመፍጠር አይደለም፡፡ የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እግዚአብሔር እኛን እንደሚወደን ማሳመኛ መንገድ አይደለም፣ ይህ የተፈጸመው ግን ገና አለም ከመፈጠሩ በፊት አባት የወደደን በመሆኑ ነው፡፡ ከክርስቶስ የመስቀል ላይ መስዋዕትነት የሚበልጥ ምን የፍቅር መግለጫ ይኖረናል?
_____________________________________________________________
______________________________________________________________
“አባት እኛን የሚወደን ስለ ታላቁ መስዋዕትነት ሳይሆን ታላቁን የዕዳ ክፍያ ራሱ ያዘጋጀው በፍቅር ስለሆነ ነው”
አንዳንዶች አባት እኛን መውደዱን ይጠራጠራል ብለው ወደ ማሰብ ያደላሉ፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስ አማላጃችን መሆኑ እርግጥ ቢሆንም አባት እኛን እንዲወደን የማሳመን ተግባር ይፈጽማል ማለት አይደለም፡፡ ክርስቶስ ራሱ እንዲህ በማለት ይህንን ስህተት የሆነ አመለካከት አስወግዷል፡፡ “አባቴ ራሱ ይወዳችኋል፡፡” (ዮሐ. 16፡27)
ሉቃ. 15፡11-24 በማንበብ የጠፋው ልጅ አባት ፍቅርን አሰላስሉ፡፡ ልጁ የአባቱን ፍቅር ያገኘባቸውን ማስረጃዎች ዝርዝር አዘጋጁ፡፡
እያንዳንዳችን በየግል መንገዳችን እንዴት ነን? እንደጠፋው ልጅ በምን አይነት መንገድ ነው እርሱን የሚመስል ልምምድ ያለን?
_____________________________________________________________
_____________________________________________________________
ረቡዕ ሰኔ 25, 2006 ዓ.ም
በርህራሄ የሚጠነቀቅልን ሰማያዊ አባታችን
ጥንቃቄ እየተደረገልን መሆኑን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለ እኛ ግድ የለሽና ቸልተኛ ቢሆኑም እንኳን፣ ሰማያዊው አባታችን በተቻለ መንገድ ሁሉ ለእኛ ይጠነቀቃል፡፡ በሰዎች ስሜት እንደተለመደው የእርሱን ምህረትና ርህራሄ የነገሮች ውጣ ውረድ አያግደውም ሁኔታዎች ምንም ዓይነት ቢሆኑ የእርሱ ፍቅር የማይለወጥና ለዘላለም የፀና ነው፡፡
ማቴ. 6፡25-34ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ሥፍራ ምን ዓይነት አጽናኝ ቃላት ይገኛሉ? በእነዚህ ቁጥሮች እንደተገለፀው የበለጠ በእግዚአብሔር ላይ መታመንን እንዴት እንማራለን?
_____________________________________________________________
_____________________________________________________________
“በልምምዳችን ውስጥ ለእርሱ ለማንበብ ጨለማ የሆነ ምዕራፍ የለም፣ ሊፈታውም ዘንድ ያልቻለው (ያስቸገረው) አንዳችም አደናጋሪ ነገር የለም፡፡ ሰማያዊ አባታችን ያላየው ወይም እርሱ በአፋጣኝ ትኩረቱን ያላደረገበት ከልጆቹ በታናሹ ላይ ያጋጠመ አንዳች ጥፋት የለም ምንም ጭንቀት ልብን አይነዘንዝም፤ ምንም ደስታ ሆነ ከከንፈር የወጣ አንዳችም ልባዊ ፀሎት እርሱ ያላወቀው የለም፡፡›› “እርሱ ልባቸው የተሰበሩትን ይጠግናል፣ ቁስላቸውንም ያክማል” መዝ. 147፡3
በእግዚአብሔርና በእያንዳንዱ ነፍስ መካከል ያለው ቅርበት አንዳችም የእርሱን ጥንቃቄና ጥበቃ የሚካፈል ነፍስ በምድር ላይ የሌለ ያህል ልጁን አሣልፎ የሰጠው ለዚያች ነፍስ ብቻ እንደሆነ ዓይነት ልዩና ሙሉ ነው፡፡” Ellen G.white-steps to Christ P.100
በዚህ ሥፍራ ካሉ ብዙ የሚያደፋፍሩ ቃላት መካከል እንኳን ቢሆን መከራ ያለና የሚጐዳን የመሆኑን እውነታ አንዘነጋም፡፡ ለዛሬ በሚሆን ጥቅስ ውስጥ “ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” (ማቴ. 6፡34) በማለት ሲናገር ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ማሳያ ነበር፡፡ ከክፋትና አሳዛኝ ከሆኑ ውጤቶቹ ጋር እንኖራለን፡፡ ዋና ነጥቡ ግን በእነዚህ ሁሉ ነገሮች መካከል፣ በብዙ መልኩ በተገለጠልን በተለይም በመስቀል ላይ በታየው፣ አባታችን ለእኛ ባለው ታላቅ ፍቅር ዋስትና ተሠጥቶናል፡፡ ሳናቋርጥ በፊታችን ያለውን የሰማያዊ አባታችንን በረከትና ሥጦታ መጠበቅ ምን ያህል አንገብጋቢ ይሆን ይህ ካልሆነ ክፉው ሁሌም እንደሚያደርገው አይቀሬ ድርጊቱ በመከራ ሲመታን በቀላሉ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡
በመከራ ጊዜ በምን ዓይነት መንገዶች ነው የእግዚአብሔርን ፍቅር እውነተኛነት ማየት የቻሉት ከዚያ ዓይነት ልምምድ ውስጥ አሁን ከችግር ጋር እየታገለ የእግዚአብሔርን ፍቅር እውነተኛነት በመጠራጠር እየጠየቀ ላለ ሰው ምን ያካፍሉታል?
_____________________________________________________________
_____________________________________________________________
ሐሙስ ሰኔ 26, 2006 ዓ.ም
አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ
ክርስቶስ በተለያዩ መንገዶች የሦስት መለኮታዊ አካላት አንድነት አምላክ (God head) እንደሆነ እነርሱም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን አስተምሯል፡፡ ይህንን እውነት በማስረጃ አስደግፎ መግለጽ ባይቻልም እንደሌሎቹ በቅዱስ ቃሉ የተገለጡ እውነቶች ሁሉ በእምነት እንቀበላለን፡፡ ከጰውሎስ ጋር አብረንም “የእግዚአብሔርን ሚስጢር ሙላት” ለመድረስ እንተጋለን (ቆለ. 2፡2) ይህም ማለት ብዙ ያላስተዋልናቸው ነገሮች ቢኖሩም በመታዘዝ በእምነትና በፀሎት የበለጠ ለማወቅ ማጥናት እንሻለን፡፡
የእግዚአብሔር ሦስቱ አካላት በክርስቶስ ህይወት ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ንቁ ተሣታፊዎች ነበሩ፡፡ በሚከተሉ ክስተቶች ውሰጥ የእያንዳንዳቸው ሚና ምን እንደነበር ይዘርዝሩ፡፡
በልደቱ ሉቃስ 1፡26-35 _________________________________________
በጥምቀቱ ሉቃስ 3፡21,22 _________________________________________
በስቅለቱ ዕብ. 9፡14 _________________________________________
የክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት ሊያበቃ በተቃረበ ጊዜ ተስፋ ለቆረጡ ደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር፡፡
በዚህም ሥፍራ ሦስቱ አካላት በህብረት ሲሰሩ እናገኛቸዋለን፡፡
“እኔም አብን እለምናለሁ “ሌላ አጽናኝ ይሠጣችኋል እርሱ ከእናንተ ጋር ለዘላለም ይኖራል እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፡፡” (ዮሐ. 14፡16-17 ቁጥር 26ን ይመልከቱ)
ክርስቶስ በማዳን እቅድ ውስጥ ከሦስቱ አካላት መካከል ፍጹም የሆነ ስምምነት እና ትብብር እንደነበር ገልጿል፡፡ ፍቅሩን ለዓለም በመግለጽ ልጅ አባቱን (አብን) እንዳከበረ (ዮሐ. 17፡14) መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ፍቅሩንና ፀጋውን ለዓለም በመግለጽ ልጁን (ወልድን) አከበረው (ዮሐ. 17፡14)
በምርምር ማስረጃ ለማቅረብ አዳጋች ስለሆኑ ሌሎች እውነቶች እያሰቡ በተመሳሳይ ሁኔታ በገሃዱ ዓለም ያሉ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮችን ደግሞ ያስቡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ ያለንን የሀሳብ ውስንነትና በእምነት ስለመኖር አስፈላጊነት ምን ይነግሩናል መልስዎትን ወደ ሰንበት ትምህርት ክፍል ያምጡ፡፡
ዓርብ ሰኔ 27, 2006 ዓ.ም
ተጨማሪ ጥናት፡- E.G white “personal God” p. 263-278, in testimonies for the church
“በእግዚአብሔር ላይ ያለንን ድፍረት (መተማመን) ለማጠንከር ከሰው ልጆች ወይም ከሰብዓዊ ዘር ልብ ጋር እጅጉን በተቆራኘ አዲስ ስም እንድንጠራው ያስተምረናል፡፡ ወሰን የሌለውን አምላክ እግዚአብሔርን አባት ብለን የምንጠራበትን ዕድል ይሠጠናል፡፡ ይህ ከእርሱ ለራሱ የተነገረለት ስም የእኛ በእርሱ የመታመናችን የፍቅራችን ማሳያ ምልክት የእርሱ ክብርና ከእኛ ጋር ያለው ህብረት ማረጋገጣ ነው፡፡ የእርሱን እርዳታና በረከት ፈልገው ሲጠሩት በጆሮው ጣዕም እንዳለው ዜማ ይሆናል፡፡
በዚህ እርሱ ራሱን ደጋግሞ በጠራበት ወይም በገለፀበት ስም መጥራት ድፍረት እንዳይመስለን፡፡ ከማዕረጉም ጋር ቅርበት ያለን እንድንሆን ይፈልጋል፡፡
“እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይመለከተናል ግድ የለሽ ከሆነው ዓለም ዋጅቶን የሰማዩ መንግሥት የልዑላን ቤተሰብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንድንሆንለት መርጦናል፡፡ ልጆች በምድራዊ አባታቸው ከሚታመኑበት እጅግ በበለጠ ሁኔታ እኛ በእርሱ ላይ እንድንታመን ይጋብዘናል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ይወዳሉ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር የሰብዓዊው ፍቅር ሊደርስበት ከሚችለው በላይ ጥልቅ፣ ሠፊና ትልቅ ነው፡፡ በፍጹም ሊለካ ከሚችለው በላይ ነው፡፡ “Ellen G-white, Christ’s object lesson P.P 141, 142
“ሰማያዊ አባታችን ፍቅሩን ለእያንዳንዳችን በጐልጐታ መስቀል ላይ ገልጿል፡፡ አባታችን ይወደናል፣ እርሱ በታላቅ ርህራሄና ምህረት የተሞላ ነው” “Ellen G-white, signs of the time, Sep 30 1889.
የመወያያ ጥያቄዎች፡-
- ከምድራዊ አባቱ ጋር ካለው ክፉ ልምምድ የተነሳ የእግዚአብሔርን ሰማያዊ አባትነትና ፍቅር ለመቀበል እየተቸገረ ያለን ሰው እርሱን እንዲወደውና ሙሉ መታመን እንዲኖረው ለማድረግ እንዴት ሊረዱት ይችላሉ?
- እግዚአብሔር እንደሚወደን እናውቃለን ታዲያ በምድር ላይ መከራ የሆነው ለምንድነው? እንደ ሰንበት ትምህርት ክፍል በሐሙሱ ቀን መጨረሻ ባለው ጥያቄ ላይ ተወያዩበት፡፡
- ሊደረስ ስለማይቻለው ዓለማት ያስቡ፡፡ ይህን የፈጠረው ያው ጌታ በመስቀል ላይ ስለመሞቱም ጭምር ያስቡ በዚህ ከማሰብ በላይ በሆነው ተስፋችን ላይ አእምሮአችንን ልናያይዝ የምንችለው እንዴት ነው? ከጊዜ ወደ ጊዜ በዚህ ሊገለጽ ከሚቻለው በላይ በሆነው የእግዚአብሔር የፍቅር ራዕይ ላይ ደስ መሰኘትን የምንማረው እንዴት ነው?